የአትሌት ጠና ነገሪ ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ

  • ቪኦኤ ዜና

Your browser doesn’t support HTML5

የአትሌት ጠና ነገሪ ሥርዐተ ቀብር ተፈጸመ

የኦለምፒክ ሯጩ ኢትዮጵያዊ አትሌት ጠና ነገሪ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ፡፡

በማራቶን ውድድር ዝናን ካተረፉ አትሌቶች አንዱ የኾነው የኦሎምፒክ ሯጩ አትሌት ጠና ነገሪ፣ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይቷል፡፡

እንደ አውሮፓውያኑ በ1992 የጃፓን ፉኮካ ማራቶን፣ በ1991 የኦል አፍሪካን ጌምስ፣ በ1994 የጣሊያን ቬኒስ ማራቶንን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች ያሸነፈው አትሌት ጠና፣ በባርሴሎና ኦሎምፒክ እና በሌሎች ዓለም አቀፍ ውድድሮች ሀገሩን ወክሎ ተወዳድሯል፡፡

አትሌቱ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ውድድሮች፣ ስምንት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ጨምሮ በድምሩ 20 ሜዳሊያዎችን ማሸነፉን ለአሜሪካ ድምፅ የደረሰው የሕይወት ታሪኩ ያስረዳል፡፡

በቀድሞው የወለጋ ጠቅላይ ግዛት በአሁኑ የኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ወለጋ ዞን ጊዳ አያና ወረዳ፣ በ1962 ዓ.ም. የተወለደው አትሌት ጠና፣ በአደረበት ሕመም በአገር ውስጥ እና በውጭ ሕክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ፣ ሚያዝያ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. በአዲስ አበባ አዲስ ሕይወት ሆስፒታል በሕክምና ላይ እያለ በ54 ዓመቱ ማረፉ ታውቋል፡፡

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በአትሌቱ ኅልፈት የተሰማውን ኀዘን ገልጿል፡፡ የአትሌቱ ሥርዓተ ቀብር፣ ዛሬ ሰኞ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ በአዲስ አበባ ሰዓሊተ ምሕረት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል፡፡

አትሌት ጠና ነገሪ ባለትዳር የነበረ ሲኾን፣ የሦስት ወንድ እና የአንድ ሴት በድምሩ የአራት ልጆች አባት ነው፡፡