ህግ አውጭዎቹ የ2 ትሪሊዮን ዶላር እቅዱን ሊነጋገሩበት ነው

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የ2ትሪሊዮን ዶላር የመሠረተ ልማት ግንባታ እቅዳቸውን ተግባራዊ ማድረግ የሚፈልጉት ትልላቆቹ የንግድ ድርጅቶች ላይ ከሚጣል ተጨማሪ የቀረጥ ገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በምስሉ የሚታየው ከአሜሪካ ጎዳናዎች አንዱ የሆነው የቺጋኮ ሃይ ዌይ 90 ነው

የዩናይትድ ስቴትስ ህግ አውጭዎች በዚህ ሳምንት ወደ ዋሽንግተን ይመለሳሉ፡፡ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ያቀረቡት የ2 ትሪሊዮን ዶላር መሰረት ልማት በጀትም ቀዳሚ አጀንዳቸው እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

ፕሪዚዳንት ጆ ባይደን በዚህ ሳምንት ከዴሞክራትና ሪፐብሊካን የጋሪዮሽ ኮሚቴዎች ጋር ተገናኝተው የአገሪቱ መንገዶችና ድልድዮች የሚሻሻሉበት፣ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ፈጣን የባቡር መስመሮች በሚዘረጉበትና በሌሎች የመሰረት ልማት ጥቅል እቅዳቸው ላይ ይነጋገራሉ፡፡

ባይደን ይህን ሲያደርጉ የሚገጥማቸው፣ በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ፣ በከኮቪድ 19 የተጎዳውን ኢኮኖሚ ለመታደግ ከጠየቁት የ1.9 ትሪሊዮን ዶላር እርዳታ ጋር ተመሳሳይ ሁኔታ ነው፡፡

ከሪፐብሊካን ፓርቲ አባላት ጋር መሰረት ልማት ሲባል ምን ምን ነገሮችን እንደሚይዝና ገንዘቡ ከየት ከየት መጥቶ እንደሚከፈል መተማመን ይጠበቅባቸዋል? ወይስ የዴሞክራቶቹን ድጋፍ ብቻ አግኘተው ወደፊት መጓዝ ይኖርባቸዋል? የሚለውም አጠያያቂ ነው፡፡

ምክንያቱም 100 አባላት ያሉት የመወሰኛው ምክር ቤት፣ 50 ዴሞክራቶች እና 50 ሪፐብሊካን የተከፈሉበት ሲሆን፣ አብላጫውን ድምጽ ለማግኘት የምክትል ፕሬዚዳንቷ ከማላ ኻሪስን ገላጋይ ድምጽ ማግኘት ይኖርባቸዋል፡፡

እስካሁን ባይደን የመረጡት የሁለቱንም ፓርቲዎች የጋራ ድጋፍ ማግኘቱን ነው፡፡

የዩናይትድ ስቴት የኃይል ምንጭ ሚኒስትር ጄኒፈር ግራንሆልም በኤቢሲ ቴሊቪዥን ላይ የባይደን ምርጫ ምን እንደሆነ እንደሚከተለው አብራርተዋል፡፤

“ እንደሚመስለው ፕሬዝዳንት ባይደን ለመደራደር ዝግጁ ናቸው፡፡ አሁን ያለው እቅድ እንደሚለወጥ ይገነዘባሉ፡፡ ይህ ሁሉንም ነገር ተደራድረህ እምትወስነበት አገር ነው፡፡ ያቀረቡት አንድ ጥቅል ጉዳይም ይሁን ዝርዝር ጉዳይ ከሪፐብሊካን አባላት ጋር መነጋገር ይፈልጋሉ፡፡”

የሪፐብሊካን መሪዎች ከወዲሁ ጥቅል እቅዱ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብን የሚጠይቅ ነው በማለት ተቃውሞቸውን ማሰማት ጀምረዋል፡፡ ባይደን እቅዱን ተግባራዊ ለማድረግ የገንዘብ ምንጭ አድርገው ያቀረቡትንም መንገድ አልተቀበሉትም፡፡

ባይደን በትላልቆቹ የንግድ ኩባን ያዎች ላይ አሁን ያለውን የ21 ከመቶ ቀረጥ በመጨመር ወደ 28 ከመቶ ለማሳደግ ያሰቡትንም ተቃውመዋል፡፡

ይህ ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከአራት ዓመት በፊት ከንግድ ድርጅቶቹ ላይ ያነሱትን ቀረጥ በከፊል ሊሽር ይችላል፡፡

ሪፐብሊካኖች ከፕሬዚደንት ባይደን ጋር ድርድሩን ማድረግ የሚፈልጉ ሲሆን ኢኮኖሚውን ከኮቪድ ወረርሽኙን ለመታደግ ከተላለፈው የኢኮኖሚው ጥቅል በጀት ወቅት ከነበረው የተሻለ ድርድር ለማድረግ ፍላጎቱ አላቸው፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

ህግ አውጭዎቹ የ2 ትሪሊዮን ዶላር እቅዱን ሊነጋገሩበት ነው

ከሚሲስፒ ግዛት የሪፐብሊካን አባል ተወካይ የሆኑት ሴነተር ሮጀር ዊከር ለኤቢሲ ቴሌቪዥን የሚከተለውን ብለዋል

“በመሰረት ልማቱ ጥቅል እቅድ ላይ ከሳቸው ጋር መደራደር እንፈልጋለን፡፡ ይህ ትሪሊዮን ዶላር ለኔ እጅግ በጣም ብዙ ነው፡፡ ያን ልነግርህ እፈልጋለሁ፡፡ ድርድር ሲባል ግን ልናድነው ከምንፈልገው እቅድ የተለየ ነገር መሆን አለበት፡፡ “

የአሜሪካ የሲቪል ኢንጂነሪን ማህበረሰብ አባላት በቅርቡ ባወጡት ሪፖርት፣ ለአሜሪካ የመሰረተ ልማት የሰጡት ደረጃ፣ የሲ ማይነስ ደረጃ መሆኑም ተመልከቷል፡፡

የኢንጂነሮቹ ቡድን ለዓመታት ተዘንግተው የቆዩት መንገዶችና ድልድዮች የተበለሻሹ ሲሆን፣ አውሮፕላን ማረፊያዎች የውሃና የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ጥገናን የሚጠይቁ ናቸው ብለዋል፡፡

የቪኦኤ ዘጋቢ ሚሸል ኲዪን ካሰናዳችው ዘገባ የተወሰደ፡፡