በሊቢያ የዋግነር ቡድን ወታደራዊ ሰፈር በድሮን ተጠቃ

የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ

“በአፍሪካ የዋግነር ቡድን ዕጣ በሀገራቱ የሚወሰን ነው” - ላቭሮቭ

በምሥራቅ ሊቢያ፣ የሩሲያው ዋግነር ተዋጊ ቡድን እንደ መሠረት የሚጠቀምበት አንድ ወታደራዊ የአየር ማረፊያ፣ የድሮን ጥቃት እንደተፈጸመበት፣ ኤኤፍፒ ከትሪፖሊ ዘግቧል።

በጥቃቱ ጉዳት አለመድረሱንና ጥቃት አድራሹም አለመታወቁን፣ አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ባለሥልጣን መናገራቸውን ዜና አገልግሎቱ ገልጿል።

ከቤንጋዚ በስተደቡብ ምዕራብ 150 ኪ.ሜ. ላይ የሚገኘው፣ አል-ካሩባ የተሰኘው ወታደራዊ የአየር ማረፊያ፣ የዋግነር ቡድን ተዋጊዎች፣ እንደ ወታደራዊ መደብ የሚጠቀሙበት ነው፤ ተብሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በልዩ ልዩ የአፍሪካ ሀገራት የሚገኘው የሩሲያው ቅጥር ወታደራዊ ቡድን ዋግነር፣ በአህጉሪቱ የሚኖረው ቀጣይ ዕጣ ፈንታ፣ ከቡድኑ ጋራ ስምምነት የተፈራረሙት መንግሥታት ውሳኔ ነው፤ ሲሉ፣ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ዛሬ አስታውቀዋል።

ዋግነር፥ ከማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እና ከሌሎችም ሀገራት መንግሥታት ጋራ፣ ሩሲያ በተፈራረመችው ስምምነት መሠረት ሲሠራ እንደነበር ላቭሮቭ ተናግረዋል። የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር፣ በመቶ የሚቆጠሩ ወታደራዊ አማካሪዎች፣ በማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ እንዳሉትም፣ ላቭሮቭ ጨምረው ገልጸዋል።

የዋግነር ቡድን፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ ለአጭር ጊዜ የቆየ ዐመፅ በማሥነሳት፣ በደቡብ ሩሲያ የምትገኝን አንዲት ከተማ ተቆጣጠሮ ነበር። ወደ ሞስኮ ሲያደርግ የነበረው ግስጋሴ ግን፣ መሪው የቭጌኒ ፕሪጎዥን፣ አገሪቱን ለቀው ወደ ቤላሩስ እንዲሔዱ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ተገትቷል።