ካማላ ሃሪስ ለአሜሪካ እና አፍሪካ አጋርነት ያላቸውን ብሩህ ተስፋ ገለጹ

Your browser doesn’t support HTML5

ካማላ ሃሪስ ለአሜሪካ እና አፍሪካ አጋርነት ያላቸውን ብሩህ ተስፋ ገለጹ

አፍሪካ እና ዩናይትድ ስቴትስ፣ የትላንት አጋሮች ብቻ ሳይኾኑ፣ የመጪውም ብሩህ ቀን የጋራ ተስፈኞች መኾናቸውን፣ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሃሪስ አመለከቱ፡፡ የአህጉሪቱ ቀዳሚ ጉዟቸውን በጋና የጀመሩት ሃሪስ፣ የወደፊቱን ተስፋ በአመለከቱበትና የትላንቱን ሕመም በአዘከሩበት የአክራ ንግግራቸው፣ ለአፍሪካ አህጉር ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል፡፡

ምክትል ፕሬዚዳንቷ ካማላ ሃሪስ በጉብኝታቸው፣ በባርነት የተያዙ አፍሪካውያን፣ በተጨናነቁ መርከቦች ውስጥ በሰንሰለት እየተቆራኙ ከቀዬአቸው ርቀው ከአትላንቲክ ማዶ ከመፈንገላቸው በፊት፣ አገራቸውን ለመጨረሻ ጊዜ ዞረው መመልከታቸውን የሚያዘክረውን የኬፕ ባሕር ዳርቻ ግንብ ተዘዋውረው ተመልክተዋል፡፡

“በዚያ ደጃፍ ያለፉ ሰዎች፥ ጠንካሮች፣ ኩሩዎች፣ ጥልቅ እምነት ያላቸው፣ ቤተ ሰዎቻቸውን የሚወዱ፣ ባህላቸውን፣ ተፈጥሯዊ ማንነታቸውን ይዘው፣ ያን ኹሉ ዘመን በመቆየት፣ በዩናይትድ ስቴትስ እና በመላው ዓለም፣ ለሲቪል መብቶች እና ለፍትሕ የታገሉ ነበሩ፡፡ ስለዚህ ኹላችንም፣ እነርሱ ለነፃነት እና ለፍትሕ በአደረጉት ትግል ተጠቃሚዎች ነን፤” ሲሉ ጥንቃቄ የተሞላበት ንግግርም አድርገዋል።

በጋና ዋና ከተማ አክራ፣ 8ሺሕ000 ለሚኾኑ ሰዎች በአሰሙት በዚኹ ንግግራቸው፣ የአህጉሪቱ የወደፊት ተስፋ አድርገው የተመለከቱትን ሲገልጹ፣ “አንድ ላይ ኾነን የመንግሥትም ኾነ የግሉ ሴክተር በራሱ ሊያሳካ ከሚችለው በላይ እጅግ የላቀ ነገር ልናሳካ እንችላለን፤” ብለዋል፡፡

“ዩናይትድ ስቴትስ እንዲህ ያለውን ትብብር በማጠናከር፣ በአህጉሪቱ የዲጂታል አሳታፊነትን ለማካተት ቁርጠኛ ናት፡፡ በመጨረሻም፣ ኹሉን አካታች የኾነ የኢኮኖሚ እድገት ለማስመዝገብ እና ቴክኖሎጂን ለማራመድ፣ በመልካም አስተዳደር እና በዴሞክራሲ ላይ ኢንቨስት ማድረጋችንንና መደገፋችን የግድ መቀጠል አለብን፤” በማለት ምክትል ፕሬዚዳንቷ አሳስበዋል፡፡

የምክትል ፕሬዚዳንቷ ጉብኝት፣ ለውጥ ማምጣቱን የገለጹት የጋና ፕሬዚዳንት ናና አኩፎ አዶ፣ “የዛሬ ከቀትር በኋላው ስብሰባ፣ በመካከላችን ዘላቂ እና ጠንካራ ትብብርን ያሳደገ መኾኑን ስገልጽ በደስታ ነው፤ ጋናም ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ በኹሉም ደረጃ ያላትን ትብብር ትቀጥላለች፤” ብለዋል፡፡

ሃሪስ፣ በአህጉሪቱ ቀዳሚያቸው የኾነውንና በጋና የጀመሩትን የምክትል ፕሬዚዳትነት ጉብኝታቸውን በማጠናቀቅ ወደ ታንዛኒያ አምርተዋል፡፡ ከዚያም ወደ ዛምቢያ እንደሚያቀኑ ተመልክቷል፡፡