የኮሮናቫይረስ አንዳንድ ቁሳቁሶች ላይ ለ28 ቀናት ሳይሞት ይቆያል

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል

ኮቪድ-19 በሽታ የሚያስከትለው ኮሮናቫይረስ እንደ መስታወት፥ የእጅ ስልክ ልባስ (ስክሪን) የማይዝግ ብረት ፥ የገንዘብ ኖት በመሳሰሉ ልሙጥነት ያላቸው ቁሶች ላይ እስከ ሃያ ስምንት ቀን ድረስ ሳይሞት ሊቆይ ይችላል ሲሉ የአውስትሬሊያ ሳይንቲስቶች ተናገሩ።

የኮመንዌልዝ የሳይንስ እና የኢንዱስትሪ ምርምር ተቋም ሳይንቲስቶች ቪሮሎጂ ጆርናል በተባለ የቫይረስ ምርመር መጽሄት ላይ ባሳተሙት አዲስ የምርምር ውጤታቸው ሳርስ ኮቭ -2 የሚባለው ቫይረስ ልሙጥነት ያላቸው ቁሳቁስ ላይ በሃያ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ሁኔታ ውስጥ ምንም ሳይሆን ይቆያል ብለዋል። ኢንፍሉዌንዛ የሚያስከትለው ቫይረስ በተመሳሳይ ሁኔታ ሳይሞት ሊቆይ የሚችለው አስራ ሰባት ቀን ብቻ መሆኑንም በመግለጽ አነጻጽረዋል።

በማያዝም ሳይንቲስቶቹ በዚህ ጥነታቸው ቫይረሱ በአርባ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ሙቀት ውስጥ ሃያ አራት ሰዓት ከቆየ በኋላ ሰውን የመያዝ አቅሙን እንደሚያጣ ገልጸዋል

በዓለማቀፉ የወረርሽኙ ይዞታ ዜናዎች የብሪታንያ ጠ/ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በሃገሪቱ በተለይም ሊቨርፑል ማንቸስተር እና ኒው ካስልን በመሳሰሉ ከተሞች የቫይረሱ ስርጭት ማሻቀቡን ተከትሎ አዲስ የቁጥጥር ገደቦችን ይፋ ሊያደርጉ መሆኑ ታውቋል።

በሃገሪቱ በተለይ በተጠቀሱት ትላልቅ ከተሞች በመሳሰሉት የቫይረሱ ተያዥ ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

በሀገሪቱ እስካሁን በኮቪድ ሳቢያ አርባ ሁለት ሸህ ስምንት መቶ ሃያ አምስት ሰዎች ሞተዋል፥ ከአውሮፓ ከፍተኛው አሃዝ ነው።

የዓለማቀፉን ወረርሽኝ ይዞታ በሚከታተለው ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ማዕከል መሰረት በዓለም ዙሪያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዘው ሰው ከሰላሳ ሰባት ነጥብ አራት ሚሊዮን አልፏል።

የሞቱ ደግሞ አንድ ሚሊዮን ሰባ አምስት ሽህ ዘጠኝ መቶ አርባ ሁለት አልፏል።