ምርጫው ሊጠናቀቅ ሶስት ሳምንታት የቀሩት ሲሆን ፕሬዚዳንታዊ እጩዎቹ ትራምፕና የዴሞክራቲክ ፓርቲ እጩ ጆ ባይደን ብርቱ ፉክክር ወደሚጠይቁት የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች በመዘዋወር ደጋፊዎቻቸውን ሊያነቃቁም ተነሳስተዋል፡፡ የቪኦኤ ሪፖርተር ኤልዛቤጥ ሊ የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅታለ፡፡
ምርጫው እየተቃረበ መጥቷል፡፡ ከፍሎሪዳ እስከ ኦሃዮ ያሉ ደጋፊዎች ከእጩዎቻቸው ዙሪያ ተሰልፈዋል፡፡ አሻሚና አፎካካሪ በሆነችው ፍሎሪዳ የፕሬዚዳንት ትራምፕ ደጋፊዎች በኮቪድ 19 ቫይረስ ከተጠቁ በኋላ፣ አገግመው ወደ ምርጫ ዘመቻው የተመለሱትን ፕሬዚዳንት ትራምፕን ለማድመጥ ወደ ስፍራው የሚያስገባቸውን የትኩሳት መጠን እየተለኩ ገብተዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ እንዲህ አሉ!
ወደ ምርጫ ዘመቻው መመለሴን በይፋ ለማወጅ ቤቴ ወደ ሆነችው ፍሎሪዳ ተመልሼ መምጣቴ ደስ ይላል!!
አገግመው ስለተነሱበት የኮረና ቫይረስም የሚከተለውን ተናገሩ
አሁንማ ኮረና አይነካህም ብለውኛል፡፡ ይሰማኛል! መጠንከሬ በጣም ይሰማኛል፡፡ ወደ ታዳሚዎቼ መራመድ እችላለሁ፡፡ ወደ መካከላችሁ መምጣት እችላለሁ፣ እዚህ ያላችሁትን ሁሉ አንድ በአንድ መሳም እችላለሁ፡፡
በኮኮቪድ 19 አይነኬ ስለመሆን ሳይንስ ግን፣ ገና እርግጠኛ አይደለም፡፡ ለማንኛውም ጆ ባይደንን ለመደገፍ በኦሃዮ የተሰባሰበው የደጋፊዎች ሁኔታ ግን የተለየ ነው፡፡ እዚያ የነበሩት የዴሞክራቲክ ፕሬዚዳንታዊ እጩ ጆ ባይደን፣ ፕሬዛዳንት ትራምፕ የኮረናቫይረስ ህመማቸውን ስለሚያስተናግዱበት ሁኔታ የሚከተለውን ብለዋል፣
ይህ እኚህ ሰው ታመውና ተመርምረው ከወጡ በኋላ እንኳ የሚያሳዩት አደገኛ ባህርይ ነው፡፡ ጨርሶ እማይገባ ነገር ነው፡፡ ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዚዳንትነቱ እየቆዩ በሄዱ ቁጥር የበለጠ አደገኛ እየሆኑ ይሄዳሉ፡፡
ትራምፕ ምናልባት ሊያሳዩ የፈለጉት ጠንካራ ሆኖ መታየትን ነው ይላሉ፣ የስታንፎርድ ዩኒንቨርስቲ ፖለቲካ ሳይንቲስት ብሩስ ኬን
“እኔ እንጃ ከዚህ በላይ በሌላ መንገድ መግለጽ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ እንዴ! በጣም ደካማ ተጠቂና ታማሚ መስለው ከታዩ እኮ ለሳቸውም ጥሩ አይደለም፡፡”
“ይሁን እንጂ” ይላሉ ኬን፣ ትራምፕ ህመማቸውንና ማገገማቸውን የሚያስተናግዱበት መንገድ ተመልሶ ሊጎዳቸው ይችላል፡፡ እንዲህ ያብራሩታል
“ለኮቪድ የሚሰጡት ምላሽ፣ ወይም ስለኮቪድ የተናገሩት በሙሉ እኔን አይነካኝም ይኸው ሊያጠቃኝ አልቻለም የሚለው አባባላቸው በአረጋውያኑ መራጮች ዘንድ እየተወደደላቸው አይመስለኝም፡፡ በተለይ በፍሎሪዳ ያሉት በርካታ ጡረተኞችና የኮቪድ ተጠቂዎች ለቫይረሱ በአደገኛ ሁኔታ የተጋለጡ ብቻ ሳይሆኑ በኮቪድ ሊሞቱ የሚችሉ ሰዎች ናቸው፡፡”
ምንም እንኳ ትራምፕ በ2106 ፍሎሪዳን ያሸነፉ ቢሆንም፣ በ2020 ግን ፍሎሪዳ አሻሚ ናት፡፡ በቅርብ የወጣው የህዝብ አስተያየት መሰብሰቢያ እንደሚገልጸው ባይደን ትራምፕን በጥቂት ይቀድማሉ፡፡ ያ ለሁለቱም እጩዎች ከፍለግዛቲቱን አሻሚ ያደርጋታል፡፡ አሁንም ብሩስ ኬይን ይህንኑ ያስረዳሉ
“ትራምፕ ለማድረግ የሚሞክሩት ነገር ደጋፊዎቻቸው ወጥተው ድምጽ እንዲሰጡ ማነቃቃት ነው፡፡ ምክንያቱም በተለይ ነጮቹ ወንዶች ወደ ምርጫው ቦታ በርከት ብለው ቢወጡላቸው፣ ከሴቶችና አረጋውያን መካከል ሊያጧቸው የሚችሉትን ድምጽ ሊያክሳክስላችው ይችላል፡፡ በባይደን የምርጫ ዘመቻ በኩልም ያለው ትኩረት በክሊንተን ጊዜ የተሠራው ስህተት እንዳይደገም ማድረግ ነው፡፡”
የላቲን አሜሪካ ዝርያ ያላቸውና ላቲኖስ የሚባሉት ከነጭ አሜሪካውያን ቀጥለው በአሜሪካ ትልቁን የመራጮችን የማህበረሰብ ክፍል ድርሻ የያዙ ናቸው፡፡ በመሆኑም በምርጫው ትልቅ ሚና ይጫወታሉ፡፡ በብሄራዊ ደረጃ ሁለት ለአንድ በሆነ ብልጫ ከትራምፕ ይልቅ ባይደንን የሚደግፉ ቢሆንም፣ በፍሎሪዳ በሚገኙና አብዛኞቹ መራጮች በሆኑት የኩባ ተወላጅ በሆኑ አሜሪካውያን ዘንድ፣ ትራምፕ የተሻለ ድጋፍ አላቸው፡፡ በአገሪቱ ለመራጮች ዋነኛ የትኩረት ጉዳይ ሆኖ የሚወጣው የኮቪድ 19 ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም መላ አሜሪካውያን ወረርሽኙን እየተፋለመች ያለቸው አገራቸው፣ በማን መመራት እንደሚገባት በድምጻቸው ያረጋግጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ቀሪውን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5