ባይደን አማንዳ ቤነትን ለዓለም ለሥራ አስፈጻሚነት አጩ

  • ቪኦኤ ዜና

አማንዳ ቤነት

ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ በጋዜጠኝነት የፑልቲዘር ሽልማት አሸናፊና፣ የቀደሞ የአሜሪካ ድምጽ ዳይሬክተርአማንዳ ቤነትን ፣ የዩናይትድ ስቴትስ ግሎባል ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አድርገው ለመሾም ማጨታቸውን፣ ዋይት ሀውስ ትናንት ዓርብ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡

ትናንት ረፋዱ ላይ “ለዚህ ስፍራ በመታጨቴ ከፍ ያለ ክብር ይሰማኛል” ያሉት ቤኔት፣ “ሹመቱ ከጸደቀ፣ በመላው ዓለም፣ የነጻ ፕሬስ እሴቶችን በመጠበቅ፣ ወሳኝና አስቸጋሪ የሆነውን የጋዜጠኝነት ሥራ ለመስራት ከሚተጉ፣ የግሎባል ኤጀንሲ ጋዜጠኞች ጋር፣ አብሬ ለመስራት ከፍ ያለ ኩራት ይሰማኛል” ብለዋል፡፡

ዜናውን ለድርጅቱ ሠራተኞች በኢሜል ያስታወቁት፣ የአሜሪካ ድምጽን ጨምሮ፣ በዓለም አቀፉ ግሎባል ኤጀንሲ ሥር የሚገኙ፣ አምስት የተለያዩ ድርጅቶችን በተጠባባቂ ሥራ አስፈጻሚነት በመምራት ላይ የሚገኙ ኬሉ ቻዎ ናቸው፡፡

የ69 ዓመቷ አማንዳ ቤኔት፣ እኤአ ከ2016 ጀምሮ ፣ እስከ ሰኔ 2020 ድረስ፣ ቪኦኤን በድሬክተርነት ሲመሩ የቆዩ ሲሆን፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕን እጩ፣ ማይክ ፓክን ፣የህግ መወሰኛው ምክር ቤት፣ የኤጀንሲው ሥራ አስፈጻሚ አድርጎ ባጸደቀበት ወቅት፣ ኃላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁ መሆኑን ይታወቃል፡፡

ዋይት ሀውስ ከቪኦኤ ለቀረበለት ጥያቄ ተጨማሪ ማብራሪያ አልሰጠም፡፡