በአሜሪካ ምርጫ በምክትል ፕሬዝደንትነት የሚወዳደሩት የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወካዩ ቲም ዋልዝ እና የሪፐብሊካን ወኪሉ ጄ ዲ ቫንስ የመጀመሪያና የመጨረሻ የተባለውን ክርክር አድርገዋል።
ሁለቱ እጩዎች መካከለኛው ምሥራቅ፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ ስደት፣ ኢኮኖሚ፣ ጽንስ የማስወረድ መብት፣ በመሣሪያ የሚፈፀም ሁከት እና ሌሎችንም ጉዳዮች በተመለከተ ተከራክረዋል።
በተለይም ማክሰኞ ኢራን በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን የሚሳዬል ጥቃት አስታኮ በመካከለኛው ምሥራቅ እየተባባሰ ያለውን ጦርነት በተመለከተ በጀመረው ክርክር፣ ጄ ዲ ቫንስ ባይደንን ለኢራን በውጪ ያለው ገንዘቧ እንዲለቀቅ በማድረጋቸው ተችተዋል።
የአሜሪካ ባላንጣዎች የሆኑት ኢራን፣ ቻይና እና ሩሲያ በባይደንና ሄሪስ ፖሊሲ ምክንያት የልብ ልብ ተሰምቷቸዋል። ያለባቸው “የአመራር እጦት” ለችግሩ ምክንያት ሆኗል ሲሉ አክለዋል ቫንስ።
ቲም ዋልዝ በበኩላቸው፣ ትረምፕ የአሜሪካ ፖሊሲ እንዳይቀጥል በማድረጋቸውና በምትኩም ሌላ ሳይተኩ በመቅረታቸው ለችግሩ ተጠያቂ ናቸው ብለዋል። በዶናልድ ትረምፕ ደካማ ፖሊሲ ምክንያት ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ለማምረት ተቃርባለች ሲሉ ከሰዋል።
“ትረምፕ የውጪ ፖሊሲን በቁም ነገር አይወስዱም” ሲሉም አክለዋል ቲም ዋልዝ።
ፍልሰትን በተመለከተ፣ ቫንስ ካመላ ሄሪስን ድንበሩን ክፍት በማድረግ የአደንዛዥ እጽ አዘዋዋሪ ቡድኖች እንዲገቡ አድርገዋል ሲሉ ከሰዋል።
ዋልዝ በበኩላቸው ትረምፕ በሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ሊጸድቅ የነበረውን የፍልሰተኞች ሕግ በማደናቀፍ ከሰዋል።
በመሣሪያ የሚፈጸም ጥቃን በተመለከተ፣ ቫንስ በትምሕርት ቤቶች ጠንካራ ጥበቃ አንዲደረግ ሲሉ ሃሳብ አቅርበዋል። የአዕምሮ ጤና ቀውስ ለችግሩ አስተዋጽኦ እንዳደረገም ጠቅሰዋል።
ዋልዝ በበኩላቸው ትምሕርት ቤቶች የጦር ካምፕ መሆን የለባቸውም ብለዋል። ወንድ ልጃቸው በትምህርት ቤት ውስጥ ተኩስ ሲከፈት መመልክቱን የጠቀሱት ዋልዝ፣ ዋና ሃላፊነታቸው ልጆችን ከአደጋ መጠበቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ትርጉም ያለውና መሣሪያ የመታጠቅን መብት የሚጠብቅ፣ እንዲሁም ልጆችንም ከአደጋ የሚጠብቅ ሕግ እንዲወጣ ጠይቀዋል።