ትረምፕና ባይደን የመጨረሻውን የምርጫ ቅስቀሳ አካሄዱ

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና ተፎካካሪያቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና ተፎካካሪያቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የመጨረሻውን የምርጫ ዘመቻቸውን በተወሰኑ አሻሚ ግዛቶች የሚገኙ መራጮችን ድምጽ ለማግኘት ሲዘዋወሩ ከርመዋል፡፡ ይህን አስመልክቶ የቪኦኤው ዘጋቢ ብራየን ፓደን ዘገባ አዘጋጅቷል፡፡

የዴሞክራቲክ ፓርቲ ተፎካካሪ እጩ የሆኑት ጆ ባይደን ከመጨረሻዎቹ የምርጫ ዘመቻዎቻቸው መካከል አንደኛውን ያሳለፉት በኦሃዮና ፐንሰልቬንያ ነው፡፡ እንዲህ ብለዋል ባይደን

“ለመነሳት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ዲሞክራሲያችንን የምናስመልስበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ይህን ማደረግ እንችላለን፡፡ እኛ እንደዚህ አይደለንም ከዚህ የተሻልን ነን!”

በህዝብ አስተያየት ድምጽ ሰብሳቢው ሪል ክሊር ፖለቲክስ መሰረት ባይደን በፐንሰልቬንያ በአራት ነጥብ እየመሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ባለፈው የ2016ቱም ምርጫ ትረምፕ በዚህን ያህል እየተበለጡም ምርጫውን አሸንፈዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ትረምፕ በበኩላቸው ባለፈው እሁድ በፍሎሪዳ የቀሰቀሱ ሲሆን ተንታኞች እንደሚሉት ትራምፕ ድል መቀዳጀት ከፈለጉ የፍሎሪዳ ግዛትን የግድ ማሸነፍ አለባቸው፡፡ ትረምፕ በፍሎሪዲ ሲናገሩ

“እንደዚህ ያለ የህዝብ ብዛት የትም አያገኙም፡፡ ማንም እንደዚህ ያለ ብዙ ህዝብ የሚያገኝ የለም፡፡ እንደዚህ ያለ ብዙ ህዝብ ሊያገኝ የሚችል ማን እንደሆነ ታውቃላችሁ አይደለም?” በማለት ጠይቀዋል፡፡

በቅርብ የተሰበሰቡ የህዝብ አስተያየት ድምጾች እንደሚያሳዩት ትረምፕ እና ባይደን በፍሎሪዳ መሳ ለመሳ ናቸው፡፡ ፕሬዚዳንት ትረምፕ ትላንት ሰኞ በኖርዝ ካሮላይና፣ ሚችጋን፣ ዊስካንሰንና በፕንሰልቬያ ተገኝተዋል፡፡ እነዚህ ክፍለግዛቶች ባለፈው የ2016ቱ ምርጫ ያሸነፉባቸው ግዛቶች ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት ግን ወይ ተቀራራቢ ይሆናሉ ወይም ወደ ባይደን ያጋድላሉ እየተባሉ ነው፡፡

ባይደን ዋነኛው ትኩረታቸው ትረምፕ በዩናይትድ ስቴትስ እንደገና ያገረሸውን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ያስተናገዱበት ደካማ መንገድ አንስቶ ማሳጣቱ ላይ አድርገዋል፡፡ ትረምፕም በበኩላቸው ከኮቪድ በፊት የነበረውን ማለፊያ የኢኮኖሚ እድገት በማንሳት ባይደን ታክስ እንደሚጨመሩና ሥራ አጥነትነት እንደሚያባብሱ ያነሳሉ፡፡ 95 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ መራጮች አስቀድመው ድምጻቸውን በተለያየ መንገድ የሰጡ ሲሆን በዚህ ዓመት የመራጮች ቁጥር በታሪክ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል ተብሎ ተገምቷል፡፡

ተንታኞች እንደሚሉት አስቀድመው ድምጽ ከሰጡት ውስጥ አብዛኞቹ ዴሞክራቶች እንደሆኑ ተነግሯል፡፡ በዛሬው እለት በብዛት ይወጣሉ የተባሉት ሪፐብሊካን ደግሞ የተፈጠረውን ክፍተት በመሙላት ትረምፕን ያግዛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በድምጽ ቆጠራው መዘገየት ሳቢያ የምርጫው ውጤት በዛሬው ምሽት ላይ ነገር የሚችልበት አጋጣሚ ሊኖር ስለሚችል አሸናፊው በእለቱ ላይገለጽ ይችላል የሚልም ነገር እየተሰማ ነው፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

ትረምፕና ባይደን የመጨረሻውን የምርጫ ቅስቀሳ አካሄዱ