የኮቪድ ክትባት በዩናይትድ ስቴትስ

  • ቪኦኤ ዜና

ፎቶ ፋይል

በዩናይትድ ስቴትስ የኮቪድ-19 ክትባት በቀጣዮቹ ሳምንታት ውስጥ ለማኅበረሰባዊ የጤና ማዕከላት ማከፋፈል እንደሚጀመር ዋይት ሃውስ አስታወቀ።

የሃገሪቱ መዲና ዋሽንግተን የፌዴራሉ መንግሥት የሚሰጣትን ክትባት በቀጥታ የምታከፋፍላቸው በቂ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ባለባቸው አካባቢዎች ለሚገኙ ሁለት መቶ ሃምሳ የአካባቢ የጤና ማዕከላትን ለይታ አዘጋጅታለች። እስካሁን የፌዴራሉ መንግሥት በቀዳሚነት ክትባት የሚያከፋፈለው ለክፍለ ሃገሮች ነበር።

ዋይት ሃውስ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በሃገሪቱ ዙሪያ ወደሰላሳ ሚሊዮን ለሚሆኑ ሰዎች አገልግሎት የሚሰጡ፣ ከአንድ ሽህ ሦስት መቶ በላይ የማኅበረሰብ የጤና ማዕከሎች እንዳሉ ገልጿል። በማያያዝም በነዚህ ማዕከሎች የሚገለገለው ህዝብ ሁለት ሦስተኛው የሚኖረው ከፌዴራል መንግሥት የድህነት ጣሪያ በታች እንደሆነ አመልክቷል። ስድሳ ከመቶውን የሚይዙት በዘር ወይም በብሄረሰብ የውህዳን ማኅበረሰብ አባላት መሆናቸውን አክሏል።

ለየክፍለ ግዛቱ የሚሰጠው የክትባት መጠንም በየሳምንቱ ከፍ እንደሚደረግ ተጠቅሷል።

የጃንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የኮቪድ-19 መረጃ ማዕከል ባለው አሃዝ መሰረት እስካሁን ድረስ አርባ ሦስት ሚሊዮን ክትባቶች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን ከኅብረተሰቡ ሦስት ከመቶው ሙሉ ክትባቱ ተከትቧል።

ጃንሰን ኤንድ ጃንሰን ኩባኒያ የቀመመው ሦስተኛው ክትባት ሲደርስ ለማኅበረሰቡ የሚከፋፈለው ክትባት ቁጥር ይጨምራል፥ ጃንሰን ኤንድ ጃንሰን ክትባቱ ለአጣዳፊ ጥቅም እንዲውል በቅርብ ጊዜ ውስጥ ፈቃድ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ዙሪያ እየተከፋፈሉ ያሉት በፋይዘር እና በሞደርና ኩባኒያዎች የተሰሩት ክትባቶች ናቸው።