የጋዛ ጦርነትን አንደኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ፣ ዩናይትድ ስቴትስ “ለፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ገንዘብ በማሰባሰብ ትልቅ ሚና ተጫውቷል” ባለችው ዓለም አቀፍ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ትስስር ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።
የዩናይትድ ስቴትስ ገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ የሐማስ ታዋቂ ዓለም አቀፍ በገንዘብ ደጋፊዎች ናቸው ብሎ በከሰሳቸው ሦስት ሰዎች፣ "ሻም" የተባለ የበጎ አድራጎት ተቋም እና ጋዛ በሚገኘው እና ሐማስ ይቆጣጠረዋል ባለው 'አል ኢንታጅ' ባንክ ላይ ማዕቀብ መጣሉን አመልክቷል።
በተጨማሪም የረጅም ጊዜ የሐማስ ደጋፊ መሆኑ የተገለጸው ቱርክ የሚኖር የመናዊ እና ዘጠኝ የንግድ ተቋማቱ ማዕቀብ እንደተጣለባቸው የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ መግለጫ አመልክቷል።
"የሐማስን አረመኔያዊ የሽብር ጥቃት አንደኛ ዓመት በምናስብበት ወቅት፣ የሐማስን እና ኢራን የአመፅ ድርጊቷን ለመፈፀም እና በገንዘብ ለመደገፍ የምትጠቀምባቸውን ሁሉ ያለመታከት የማዳከም ስራውን ይቀጥላል" ያለው የሚኒስትሩ መግለጫ፣ ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሲሉ ሁኔታውን የሚጠቀሙበትን ጨምሮ፣ ሐማስን እና ደጋፊዎቹን ተጠያቂ ለማድረግ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስትር የሚችለውን ሁሉ እንደሚያደርግ አመልክቷል።
"ሐማስ ሰላማዊ ዜጎችን እንረዳለን የሚሉ ሀሰተኛ በጎ አድራጎት ድርጅቶችን በመጠቀም ጋዛ ውስጥ የሚደርሰውን ስቃይ መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን" የገለጸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከዚህ ዓመት መግቢያ ጀምሮ ቡድኑ በወር እስከ 10 ሚሊየን ዶላር ድረስ በልገሳ ተቀብሎ ሊሆን እንደሚችል ጠቅሷል። በተጨማሪም ሐማስ አውሮፓን ቁልፍ የገንዘብ መሰብሰቢያ ምንጭ አድርጎ እንደሚመለከታት ጠቅሷል።
ዩናይትድ ስቴትስ ዛሬ ሰኞ በወሰደችው እርምጃ መቀመጫውን ጣሊያን ያደረገ የሐማስ አባል እንደሚገኝበት እና አባሉ ያቋቋመው ሻም የተሰኘ በጎ አድራጎት ማህበር የሐማስን ወታደራዊ ክንፍ እንደሚረዳ ተመልክቷል።
ጀርመን የሚገኝ የሐማስ ወኪል እና ኦስትሪያ የሚገኝ የቡድኑን እንቅስቃሴ የሚመራ ወኪልም እንዲሁ በማዕቀቡ ዒላማ መደረጋቸው ተገልጿል።