በአፍጋኒስታን ለ17 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በፖለቲካ ድርድር ለማብቃት በዩናይትድ ስቴትስና በታሊባን መካከል ኳታር ውስጥ የሚካሄደው የሰላም ንግግር መቀጠል ትልቅ ተስፋ አሳድሯል።
ዋሺንግተን ዲሲ —
በአፍጋኒስታን ለ17 ዓመታት የዘለቀውን ጦርነት በፖለቲካ ድርድር ለማብቃት በዩናይትድ ስቴትስና ባታሊባን መካከል ኳታር ውስጥ የሚካሄደው የሰላም ንግግር መቀጠል ትልቅ ተስፋ አሳድሯል።
ንግግሩ ባሳለፍነው ሰኞ ሲጀመር የዩናይትድ ስቴትሱን ልዑካን ቡድን የመሩት የዋሺንግተኑ ልዩ ተወካይ ዛልሜ ኻሊዛድ ናቸው።
የፓኪስታንና ካታር ልዑካንም በመክፈቻው ተገኝተዋል።
የሰላም ንግግሩ ዛሬ ለአራተኛ ቀን የቀጠለ ሲሆን ወገኖቹን ብዙ ባለያዩ ሁለት ጉዳዮች ላይ እድገት መታየቱን በጣም ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።
ታሊባን ንግግሩ እንደተጀመረ ቀድሞ ያቀረበው ጥያቄ፣ የዩናይትድ ስቴትስና በኔቶ የሚመራው ወታደራዊ ጥምረት ከአፍጋኒስታን ጠቅልሎ የሚወጣበት የጊዜ ሰሌዳ እንዲሰጠው ነው። ያ ከሆነ የአፍጋኒስታን ምድር አሜሪካንንም ሆነ ሌሎች ሃገሮች ለማስፈራራት መጠቀሚያ እንደማይውል ታሊባን ማረጋገጫ እሰጣለሁ ብሏል።
የአፍጋኒስታን ነውጠኛው የታሊባን ቡድን የፖለቲካ ጽሕፈት ቤት የሚገኘው በዶሃ መሆኑ ይታወቃል።