የሻይራት ድብደባና የዓለም ምላሽ

US Syria

ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ሌሊት በአንድ የሶሪያ የአየር ኃይል መደብ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት የአውሮፓ አጋሮቿ ሲደግፉ ሩሲያ የወረራ አድራጎት ነው ስትል አውግዛዋለች፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ሌሊት በአንድ የሶሪያ የአየር ኃይል መደብ ላይ ያደረሰችውን ጥቃት የአውሮፓ አጋሮቿ ሲደግፉ ሩሲያ የወረራ አድራጎት ነው ስትል አውግዛዋለች፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ የሚሣይል ድብደባውን የፈፀመችው ከሁለት ቀናት በፊት የሶሪያው ፕሬዚዳንት ባሻር አል አሳድ ኃይሎች በአማፂያን በተያዘችው ኢድሊብ ከተማ ላይ ላደረሱት የኬሚካል ጦር መሣሪያ ድብደባ አፀፋ መሆኑን ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል፡፡

በኬሚካል ጥቃቱ መቶ የሚሆኑ ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል፡፡

ያለፈው ሌሊት ድብደባ ዩናይትድ ስቴትስ በሶሪያ መንግሥት ኃይሎች ላይ በቀጥታ የሠነዘረችው የመጀመሪያ ጥቃት ነው፡፡

ከማለዳው አሥር ሰዓት ከአርባ ደቂቃ ላይ የሜዲቴራኒያን ሰማይ እጅግ በደመቁ የብርሃን ኳሶች ተጨናነቀ፡፡ ወዲያውም የሦሪያይቱ ምዕራባዊ ከተማ ሻይራት የእሣት የአየር ኃይል መደብ የእሣት ዝናብ ወረደበት!! ሜዲቴራኒያን ባሕር ላይ የሚገኙ ሁለት የባሕር ኃይሉ አውዳሚ መርከቦች ሃምሣ ዘጠኝ ቶማሆክ ተምዘግዛጊ ሚሣይሎችን ያለማቋረጥ አወረዱ፡፡

ከድብደባው በኋላ የዩናይትድ ስቴትሱ መሪ የቻይናውን ፕሬዚዳንት ሲ ጂንፒንግን እያስተናገዱ ባሉባት ደቡባዊቱ ግዛታቸው ፍሎሪዳ ከማር-አ-ላጎ መዝናኛ ለጋዘጠኞች በሰጡት መግለጫ ወታደራዊውን እርምጃ ማዘዛቸውን አስታውቀዋል፡፡

ድብደባውን ለዩናይትድ ስቴትስ ብሄራዊ ደኅንነት ሲባል የታዘዘ መሆኑንም ተናግረዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

«በሦሪያ የኬሚካል መሣሪያ ጥቃት ለማድረስ በተነሡበት የአየር ኃይል መንደርደሪያ ላይ ያነጣጠረ ወታደራዊ ጥቃት እንዲፈፀም በዚህ ምሽት አዝዣለሁ፡፡ ድብደባው ገዳይ የሆኑ ኬሚካል መሣሪያዎችን ሥርጭት ለመቆጣጠርና ለማቆም ለዩናይትድ ስቴትስ ቁልፍ ብሄራዊ ደኅንነት ሲባል የተወሰደ እርምጃ ነው» ብለዋል፡፡

የሦሪያ መንግሥት ኃይሎች በአማፂያን በተያዘችው ኢድሊብ ላይ አድርሰዋል የተባለውን ሳሪን እንደሆነ የተነገረ የመርዝ ጋዝ ጥቃት «ሥልጣኔ እጅግ የጎደለውና አረመኔያዊ» ሲሉ ጠርተውታል፤ ፕሬዚዳንት ትረምፕ፡፡

«ረዳት የሌላቸውን ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናትን ሕይወት አፍኖ ነጥቋል» ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፤

ትረምፕ አክለውም የሶሪያውን ፕሬዚዳንት ባሻር አል-አሳድን ምግባርና ጠባይ ለመለወጥ ቀደም ሲል ለዓመታት የተደረጉ ጥረቶች ሳይሳኩ ቀርተዋል ብለው ሦሪያ ውስጥ ያለው መከራ እንዲያበቃ ለማድረግ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ አብሯቸው እንዲሆን ጠይቀዋል፡፡

«ሶሪያ ውስጥ ያለው ግድያና የደም መፍሰስ እንዲያበቃ፣ በማንኛውም ሁኔታና መንገድ የሚከሰት ሽብር ፈጠራ እንዲያከትም ለማድረግ የሰለጠኑ መንግሥታት ሁሉ ከጎናችን እንዲቆሙ እንጠይቃለን» ብለዋል፡፡

የአሜሪካን ጥቃት «የወረራ አድራጎት» ሲል የሶሪያ ቴሌቪዥን ጠርቶታል፡፡

የባሕር ኃይላቸው ያደረሰውን ድብደባ እንደሚያዝዙ ፕረዚዳንት ትረምፕ ቀድመው ባያሳውቁም እርሣቸውና ሌሎች የፀጥታ ባለሥልጣኖቻቸው በሦሪያ መንግሥት ላይ ቀኑን ሙሉ ዛቻ ሲያሰሙ ውለዋል፡፡

ዶናልድ ትረምፕ ሌሊቱን የወሰዱት እርምጃ ቀደም ሲል እንደ ዕጩም እንደ ተመራጭ ፕሬዚዳንትና በኋላም ፕሬዚዳንት ሆነው ከያዙት ለሰባት ዓመታት በዘለቀው የሦሪያ የርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የአሜሪካን ተጎትቶ መግባት ከሚቃወሙበት አቋማቸው አስደናቂ የሆነ መታጠፍ እንደሆነ እየተነገረ ሲሆን የአሁኑን ጥቃት እንዲፈፅሙ ያነሳሳቸው በኬሚካል ጥቃቱ የተገደሉ ሕፃናትን የሚያሳዩ ፎቶዎችና ቪድዮዎችን ማየታቸው መሆኑ ተዘግቧል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

የሻይራት ድብደባና የዓለም ምላሽ

ያንን የኬሚካል መሣሪያ ጥቃት «ለሰው ልጅ ውርደት» ሲሉ ጠርተውታል፡፡ የሦሪያ መንግሥትም «መተላለፍ የማይገባውን ብዙ መሥመሮች የጣሰበት» አድራጎት እንደሆነም ተናግረዋል ትረምፕ፡፡

እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ፈረንሣይ፣ ሳዑዳ አረቢያ፣ እሥራኤል ጃፓን ዋሺንግተን የፈፀመችውን ድብደባ እንደሚደግፉ በይፋ ተናግረዋል፡፡ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ መርከል፣ የፈረንሣይ ፕሬዚዳንት ፍራንሷ ኦሎ፣ የእሥራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ለእርምጃው ያላቸውን ድጋፍ ያሳወቁት ያለ ቃል አቀባይ ነው፡፡

የቱርክ ፕሬዚዳንት ራቺፕ ኤርዶዋንም በሶሪያው አገዛዝ ላይ ይበልጥ ጠንካራ የሆኑ እርምጃዎችን ለመውሰድ ከዋሺንግተን ጋር ለመሥራት ዝግጁ መሆናቸውን አሳውቀው ሩሲያ ለደማስቆ እየሰጠች ስላለችው ድጋፍም ወቀሳ አሰምተዋል፡፡

ኢራን ድብደባውን በብርቱ አውግዛ «በተናጠል የሚወሰድ እርምጃ አደገኛ፣ አሰናካይና የዓለምአቀፍ ሕግን መርኆች የሚጥስ ነው» ብላለች፡፡

ለአሳድ መንግሥት የወታደሮችና የአየር ድጋፍ የምትሰጠው ሩሲያ የዩናይትድ ስቴትስን ወታደራዊ እርምጃ አውግዛ «የወረራ አድራጎት» ስትል ጠርታዋለች፡፡

የውል ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ ቃል አቀባይ ማሪያ ሳኻረቫ ሞስኮ ላይ በሰጡት መግለጫ «እንዲህ ዓይነቱ አድራጎት ቀደም ሲል ሽብር ፈጠራን መዋጋት ነው ይባል ከነበረ አሁን ግን ይህ በሉዓላዊቱ ሶሪያ ላይ የተፈፀመ ግልፅ የወረራ አድራጎት ነው» ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ግን ሁሉም ወገኖች ችግሮችን ለመፍታት ከፖለቲካዊ መፍትኄዎች ጋር ብቻ እንዳጣበቁ የቻይና የውግጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ አሳስቧል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

የሻይራት ድብደባና የዓለም ምላሽ