የጋዛን ጦርነት ተከትሎ በአካባቢው ውጥረቱ እየተባባሰ ባለበት በዚህ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ የመን ውስጥ ለመብረር እየተዘጋጁ የነበሩ 10 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መምታቷን ትናንት ረቡዕ አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣን ተናገሩ፡፡
ከዚያም ሌላ የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኅይል በአደን ባሕረ ሰላጤ ሦስት የኢራን አብራሪ አልባ አውሮፕላኖችን እና የየመን ሁቲዎች ጸረ መርከብ ተወንጫፊ ሚሳይል ተኩሶ መጣሉን የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኅይል ማዕከላዊ ዕዝ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡ በጥቃቱ በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሶ እንደሆን መረጃ እንደሌለ መግለጫው አክሎ አመልክቷል፡፡
አብዛኛውን የየመን ግዛት የሚቆጣጠሩት በኢራን የሚታገዙት ሁቲ ታጣቂዎች በቅርብ ሳምንታት በቀይ ባሕር እና በአደን ባሕረ ሰላጤ በሚያልፉ መርከቦች ላይ በተደጋጋሚ በሰው አልባ አውሮፕላን አና በሚሳይል ጥቃት ሲያደርሱ ቆይተዋል፡፡ ጥቃቱን የሚፈጽሙት እስራኤል ጋዛ ውስጥ የምታካሂደውን ወታደራዊ ዘመቻ ለመቃወም እና ለፍልስጥዔማውያን ድጋፋቸውን ለመግለጽ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ሁቲ ታጣቂዎች የሚያደርሱት ጥቃት ዓለም አቀፍ የጭነት መርከብ እንቅስቃሴዎችን ያስተጓጎለ ሲሆን ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታኒያ የመን ውስጥ ባሉ የሁቲዎች ይዞታዎችን አጥቅተዋል፡፡ ቡድኑንም ሽብርተኛ ቡድኖች መዝገብ ውስጥ መልሰው ከትተውታል፡፡
ትናንት ረቡዕ ሁቲዎቹ በዩናይትድ ስቴትስ ባህር ኅይል አውዳሚ መርከብ ላይ ጥቃት ካደረሱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ “ የባሕር ኅይላችን በአደን ባሕረ ሰላጤ በዩናይትድ ስቴትስ የንግድ መርከብ ላይ እርምጃ ወስደዋል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የየመን ሁቲዎች በቀይ ባሕር እና አካባቢው የሚያደርሱት ጥቃት በእስያ እና በአውሮፓ መካከል የሚደረገውን የንግድ እንቅስቃሴ እያጓተተ ሲሆን የአቅርቦት ዕጥረት ይመጣል የሚል ስጋት ተፈጥሯል፡፡ ከዚያም ሌላ ኅያላኑ ሀገሮች ዘንድ የጋዛው ጦርነት ወደቀጣናዊ ግጭት ሊሸጋገር ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል፡፡
በቅርቡ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ሲናገሩ ሁቲዎቹ ጥቃት ማድረሳቸውን ላያቆሙ እንደሚችሉ ቢያምኑም የቡድኑን ዒላማዎች የሚካሄደው ጥቃት እንደሚቀጥል መናገራቸው ይታወሳል፡፡