ሰሜን ኮሪያ፣ ሩስያ ዩክሬን ውስጥ እያካሄደች ያለችውን ጦርነት በመደገፍ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችቿን ወደ ሥፍራው መላኳን ተከትሎ እና ፒዮንግያንግ በኒውክሌር ፕሮግራሟ አማካኝነት ለደቀነችው አደጋ የተባበረ ምላሽ ለመስጠት በታለመ እቅድ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዛሬ አርብ ከደቡብ ኮሪያ እና ከጃፓን አቻዎቻቸው ጋር ተገናኝተው እንደሚነጋገሩ ተገለጠ። ሶስቱ መሪዎች የሚወያዩት ሊማ ፔሩ ላይ ከሚካሄደው የእስያ-ፓሲፊክ የምጣኔ ሃብት ትብብር መድረክ ትይዩ መሆኑም ታውቋል።
ፒዮንግያንግ ጦሯን በዩክሬይን ማሰማራቷ “ትልቅ ክብደት የሚሰጠው እርምጃ ነው” ሲሉ የመሪዎቹን ጉባኤ ለመዘገብ ከፕሬዝዳንቱ ጋር ወደ ሊማ በመጓዝ ላይ ለነበሩት ጋዜጠኞች የተናገሩት የዋይት ሀውሱ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳዮች አማካሪ ጃክ ሱሊቫን፤ “ጉዳዩ ክብደት በሚመጥን ትኩረት ምላሽ እንሰጠዋለን" ብለዋል።
ሱሊቫን አክለውም “የሶስትዮሹ ጉባኤ፤ መሪዎቹ ዩናይትድ ስቴትስ በመጭው የጥር ወር አጋማሽ የአስተዳደር ሽግግር ለማድረግ በዝግጅት ላይ ባለችበት ወቅት፤ የኒውክሌር ሙከራዎችን እና የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፍን ጨምሮ ፒዮንግያንግ ለምትቃጣቸው ማናቸውም “የትንኮሳ” ድርጊቶች እንዲዘጋጁ ያስችላቸዋል” ብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ የአስተዳደር ለውጥ የሚደረግበት ወቅት በታሪክ ፒዮንግያንግ የትንኮሳ ድርጊቶች ለማድረረግ የምትመርጠው ጊዜ መሆኑን ሱሊቫን አስታውሰዋል።
የሶስትዮሹ ጥረት፣ ባይደን ሶል እና ቶኪዮ ለዓመታት የዘለቀውን በባላንጣነት ከሚተያዩበት ግንኙነት ተሻግረው፤ የጋራ ተገዳዳሪዎቻቸው የሆኑትን የሰሜን ኮሪያን እና የቻይናን ተጽዕኖ ለመመቋቋም የሚያስችል ጥምረት የመሰረቱበት በቀጣናው ካቋቋሟቸው ቁልፍ-ቁልፍ የደህንነት እርምጃዎቻቸው አንዱ ነው።
ትራምፕ በአንጻሩ በመጀመሪያ የስልጣን ዘመናቸው ከሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ጋር ወዳጅነት ለማበጀት ካደረጉት ጥረት በተጨማሪ፤ ቶኪዮ እና ሶል ለዩናትድ ስቴትስ የጦር ኃይል ወጭ ከሚደረገው ዳጎስ ያለ ድርሻ እንዲጋሩ ግፊት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በሌላ በኩል፡ ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ከመመረጣቸው አንድ ቀን ቀደም ብሎ፣ ደቡብ ኮሪያ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጣር በ2026 የበጀት ዓመት በአገሯ የተሰማራውን የአሜሪካ ጦር ሠራዊት ወጭ ለመደገፍ የሚውለውን ክፍያ ወደ 1.19 ቢሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አዲስ ስምምነት ተፈራርማለች። ይህም ባለፈው ዓመት ከነበረው የ8.3 በመቶ ጭማሪ መሆኑ ታውቋል።