የአሜሪካ ኒውክሌር ጫኝ መርከብ ከደቡብ ኮሪያ ጋር ለሚደረግ ወታደራዊ ልምምድ ቡሳን ወደ የተባለችውን የአገሪቱ የወደብ ከተማን በዚህ ሳምንት እንደሚጎበኝ በደቡብ ኮሪያ የአሜሪካ ባህር ኃይል አስታውቋል።
ሰሜን ኮሪያ በቅርቡ የኒውክሌር ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ስለምትገኝ፣ አሜሪካና አጋሮቿ ኃይላቸውን ለማሳየት ያለመ ጉብኝንት ነው ሲል የቪኦኤው ዊሊያም ጋሎ ከሶል ደቡብ ኮሪያ ዘግቧል።
ዩኤሴኤስ ሮናልድ ሬገን የተባለቸው ኒውክሌር ጫኝ መርከብ ዓርብ እንደምትደርስ እየተጠበቀ ሲሆን፣ የደቡብ ኮሪያ ባህር ኃይል ባወጣው መግለጫ እንዳለው ሁለቱ ወገኖች “የጦር ዝግጁነታቸውን የሚያሳዩበት እንዲሁም አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ በትብብሩ ለሰላምና መረጋጋት ያላቸውን ፍላጎት የሚያሳዩበት ነው” ብሏል።
በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን መካከል ውጥረት አይሎ ከነበረበት ከእአአ 2017 ወዲህ ሁለቱ ሀገሮች እንዲህ ዓይነት ትብብር ሲያደርጉ ለመጀመሪያ ግዜ መሆኑ ታውቋል። አሁን ከአምስት ዓመታት በኋላ ውጥረቱ እንደገና አገርሽቷል። ሁለቱም ወገኖች ወታደራዊ ኃይላቸውን በማሳየት ላይ ናቸው ሲል ዊሊያም ጋሎ በዘገባው አመልክቷል።
ሰሜን ኮሪያ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ ከዚህ በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃጸር ከፍተኛ ቁጥር ያለው የኑክሌር ሙከራ ያደረገች ሲሆን፣ የአሜሪካና የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ሰባተኛውን ሙከራ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ነች።
የኒውክሌር ፕሮግራማቸውን እንደማይተውና በድርድር ወቅት እንደ ማስፈራሪያ እንደሚጠቀሙበት የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።
ሰሜን ኮሪያ በተጨማሪም ከጠላቶቿ ጥቃት ቢደርስባት ወዲያውኑ በኒውክሌር ኃይል ምላሽ እንደምትሰጥ የሚደነግግ ህግ አውጥታለች።
አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ ይህን አውግዘው ከሰሜን ኮሪያ ለሚመጣ የኑክሌር ጥቃት “ከባድና ወሳኝ መልስ” እንደሚሰጡ ዝተዋል።
ደቡብ ኮሪያ የራስዋ የኒውክሌር ኃይል የላትም። “የኒውክሌር የጃንጥላ ከለላ” ብለው አሜሪካኖቹ በሚጠሩት ፕሮግራም ታቅፋለች።
አሜሪካ በደቡብ ኮሪያ 28 ሺህ 500 ወታደሮች አሏት።