የዩናይትድ ስቴትስ በደቡብ ሱዳን ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ ጣለች

የዩናትይድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

ዩናይትድ ስቴትስ የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ፣ ለሰብአዊ ርዳታ እጅግ ደሃ ወደ ሆነቸው ሀገር እንዳይገባ እንቅፋት ሆነዋል ባለቻቸው ቁጥራቸው በውል ባልታወቀ ደቡብ ሱዳናውያን ላይ የቪዛ ማዕቀብ መጣሏን ዛሬ ዓርብ አስታወቀች፡፡

የዩናትይድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ “እኤአ በ2011 ነጻነቷን ከሱዳን የተቀዳጀችው ደቡብ ሱዳን ለአምስት ዓመት የዘለቀው የርስ በርስ ጦርነት እኤኤ በ2018 በተካሄደው የሰላም ስምምነት ካበቃ በኋላ የደቡብ ሱዳን አስተዳደር በሙስና እና በጎሳ ግጭት እየተናጋ ነው።ብሏል፡፡

“እነዚህ ግለሰቦች ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ለመግባት ብቁ ላይሆኑ ይችላሉ” ያለው ዩናትይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፣ ምንም እንኳ ማዕቀብ የተጣለባቸውን ግለሰቦች በስማቸው ባይገልጽም፣ ግለሰቦቹ “የህይወት አድን ሰብአዊ እርዳታዎችን ሥራ በማደናቀፍ እና የርዳታ ጭነቶችን ቀረጥ በማስከፈል ተሳትፈዋል” ብሏል፡፡

መግለጫው አክሎም እ.ኤ.አ. በ2018 የተቋቋመው የደቡብ ሱዳን የሽግግር መንግስት በሰላም ስምምነቱ ውስጥ ያሉትን ግዴታዎች ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስርዓት ለመዘርጋት ባለመቻሉ ዩናይትድ ስቴትስ “በጣም አሳስቧታል” ብሏል።

በተለይም መንግስት ሰብዓዊ ርዳታዎችን ለማድረስ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ መፍጠር እንዳለበትመግለጫው ጠቁሟል።

እ.ኤ.አ. በ2018 የተደረሰበት ስምምነት ለስልጣን ክፍፍል መንገዱን የጠረገ ሲሆን የፖለቲካ ሽግግር እና የምርጫ ፍኖተ ካርታ ዘርግቷል።

ነገር ግን እ.ኤ.አ ነሀሴ 2022፣የደቡብ ሱዳን መሪዎች የሽግግሩን ጊዜ ለተጨማሪ 24 ወራት ማለትም ወደ የካቲት 2025 ለማራዘም በመስማማታቸውምርጫው በዚህ ዓመት ታህሣሥ 22 እንዲደረግ ጊዜያዊ የጊዜ ሰሌዳ ተቀምጧል።

ይሁን እንጂ ብሔራዊ ሕገ መንግሥት መፍጠርን ጨምሮ የስምምነቱ ቁልፍ መርሆች አሁንም ያልተሟሉ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡