የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ትላንት ብራስልስ በተካሄደው የአውሮፓ ኅብረት ስብሰባ ላይ በመገኘት ከኅብረቱ ጋራ ለተፈረመው የረዥም ጊዜ የፀጥታ ስምምነት አባል ሃገራቱን አመስግነው፣ ቃል የተገባው ወታደራዊ ርዳታም በአስቸኳይ እንዲሰጥ ጠይቀዋል።
የአውሮፓ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ቻርለስ ሚሼል እና የአውሮፓ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሰላ ቮን ደር ላየን ከዜለኒስኪ ጋራ በመሆን ስምምነቱን ተፈራርመዋል።
ዩክሬን ሦስት ዓይነት የፀጥታ ስምምነት ተፈራርማለች። የመጀመሪያው በአጠቃላይ ከአውሮፓ ኅብረት ጋራ ሲሆን፣ ሌሎቹ ሁለቱ ደግሞ ከሊትዌኒያ እና ኢስቶኒያ ጋራ መሆኑ ታውቋል።
ዜለንስኪ ወደ ስብሰባው ከማቅናታቸው በፊት በ X ማኅበራዊ ገጻቸው ላይ ባሠፈሩት መልዕክት፣ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁሉንም የኅብረቱ 27 ሃገራት ያካተተ ስምምነት መሆኑን እና በተቋሙ ውስጥ ለውጥ ቢኖር እንኳ፣ ዩክሬን ቀጣይ እገዛ የምታገኝበት ሁኔታን እንደፈጠረ አስታውቀዋል። በሩሲያው ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ላይ ተጨማሪ ጫና መፍጠር እንደሚያስፈልግም በውይይቱ ወቅት ተናግረዋል።