ሩሲያ ምስራቃዊ እና ሰሜን ምስራቃዊ ሞስኮ አቅራቢያ ባሉ ሁለት ክፍለ ግዛቶቿ ሲበርሩ የነበሩ የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖችን መትታ መጣሏን ተናገረች፡፡ አካባቢዎቹ የዩክሬይን ኃይሎች አዘውትረው ዒላማ የሚያደርጓቸው እንዳልሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አንደኛውን ድሮን ያሮስላቪ ክፍለ ግዛት ሁለተኛውን ደግሞ ቪላዲሚር ክፍለ ግዛት ውስጥ መትታ እንደጣለች ሩሲያ አስታውቃለች፡፡ በድሮኑ ስብርባሪ በሰው ላይም ይሁን በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የያሮስላቭ አገረ ገዢ ገልጸዋል፡፡ ዩክሬይን በጥቃቶቿ አእብዛኛውን ጊዜ የምታነጣጥረው በሚያዋስኗት የሩስያ ግዛቶች ላይ ነው፡፡
የዩክሬይን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ከቡድን 7 አባል አገሮች መሪዎች ጋር ለመነጋገር ወደጣሊያን ተጉዘዋል፡፡ ዜሌንስኪ በንግግራቸው በቀዳሚነት ከሚያተኩሩባቸው ጉዳዮች መካከል ለዩክሬይን ኅይሎች የአብራሪ ስልጠና እንዲሰጥ ተዋጊ ጀቶች በአፋጣኝ እንዲላኩ እና የረጅም ርቀት ጥቃት አቅሟ እንዲጠናከር የሚሉት እንደሚገኙበት አስታውቀዋል፡፡
የዩክሬይን የመከላከያ ሚንስትር ሩስቴም ኡሜሮቭ ከሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሀገሮች አቻዎቻቸው ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸው ተዘግቧል፡፡ የኔቶ ዋና ጸሐፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ የሕብረቱ ሀገሮች ለዩክሬይን ስለሚላክ የአየር ጥቃት መከላከያ መሣሪዎች እርዳታ በቀጣዮቹ ቀናት እና ሳምንታት ይፋ ያደርጋሉ ብለው እንደሚጠብቁ አመልክተዋል፡፡