የዩክሬን ሰሜናዊ ግዛት በሩሲያ ሚሳዬሎች መጠቃቱን ባለሥልጣናት ተናገሩ

  • ቪኦኤ ዜና
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ የነፍስ አድን ሠራተኞች በሥራ ላይ በዩክሬን፣ በቼርኒሂቭ፣ እአአ ሚያዚያ 17/2024

ሩሲያ ዩክሬን ላይ ጥቃት ካደረሰች በኋላ የነፍስ አድን ሠራተኞች በሥራ ላይ በዩክሬን፣ በቼርኒሂቭ፣ እአአ ሚያዚያ 17/2024

የዩክሬን ባለሥልጣናት ሰሜናዊቷ ቼርኒሂቭ ከተማ በሩሲያ ሚሳዬል ጥቃት መመታቷን ዛሬ ረቡዕ ተናገሩ፡፡

የቼርኒሂቭ ከንቲባ አሌክሳንደር ሎማኮ በጥቃቱ ቢያንስ 16 ሰዎች ሲገደሉ 18 ሰዎች ቆስለዋል ሲሉ በማኅበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጽ "ቴሌግራም" ላይ አስፍረዋል።

በመሀል ከተማው አቅራቢያ የሚገኙ አካባባቢዎች በሚሳዬሎች መመታታቸውን ፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ይቼስላቭ ቻውስ ተናግረዋል። በርካታ ያልታጠቁ ሰዎች በጉዳቱ መቁሰላቸውን ቻውስ ገልፀዋል።

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ዜለነስኪ በጥቃቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ሐዘናቸውን ገልጸው አጋሮቻቸው ዩክሬንን ከሩሲያ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እና የሚሳዬል ጥቃቶች ለመከላከል የበለጠ እገዛ እንዲያደርጉ በድጋሚ አሳስበዋል፡፡

በሌላም በኩል የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ሞርዶቪያ ክልል ላይ የዩክሬንን ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መደምሰሱን ዛሬ አስታውቋል፡፡

ዜሌነስኪ ሁኔታውን በቅርብ ቀናት ውስጥ እስራኤልን ከኢራን ሰው አልባ አውሮፕላኖችና ከሚሳዬል ጥቃቶች ለመከላከል ከሚደረገው ሁለገብ ጥረት ጋር አነጻጽረዋል፡፡

“ዩክሬን በቂ የአየር መከላከያ መሳሪያዎችን ብታገኝ እና ዓለም የሩሲያ ሽብርተኝነትን ለመከላከል ያለው ቁርጠኝነት በቂ ቢሆን ኖሮ ይህ አይከሰትም ነበር" ያሉት ዜለነስኪ "አሸባሪዎች ህይወትን ሊያጠፉ የሚችሉት ሽብርን ለማስቆም እና ህይወትን የሚያድኑትን በመጀመሪያ ሲያስፈራሩ ብቻ ነው። ውሳኔ አስፈላጊ ነው። ድጋፍ ወሳኝ ነው።” ብለዋል፡፡

በኢንዱስትሪ ከበለጸጉት የቡድን ሰባት ሀገራት አቻዎቻቸው ጋር ጣሊያን ውስጥ በሚደረገው ስብሰባ እየተሳተፉ የሚገኙት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አነቶኒ ብሊንክን ቻይና ለሩሲያ መከላከያ ኢንደስቱሪ የምታደርገውን ድጋፍ በተመለከተ የአሜሪካን ስጋት አንስተው እንደሚወያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴራቸው ገልጿል፡፡

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር ትላንት ማክሰኞ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ባለፉት ወራት ዩናይትድ ስቴትስ ከቻይና ወደ ሩሲያ የተዘዋወሩ ቁሶችን መመልከቷን ተናግረዋል፡፡

ሩሲያ “ቁሳቁሶችን የመከላከያ ኢንዱስትሪዋን እንደገና ለመገንባት እና በዩክሬን ጦር ሜዳ የሚታዩ መሳሪያዎችን ለማምረት እየተጠቀመችበት ነው” ብለዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ጉዳዩ ያሳሰባትና ከቻይና ጋራ ስትነጋገርበት የቆየች መሆኑን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡

የውጭ ጉዳያ ሚኒስትሩ ብሊከን “ በመጭዎቹ ሳምንታት ወደ ቻይና ለመጓዝ እቅድ አላቸው” ያሉት ቃል አቀባዩ ጉዳዩ “ያነሱታል ተብሎ የሚጠበቅ ነው” ሲሉም አክለዋል፡፡