የዩክሬንን እህል ወደ ውጭ የመላኩ ሥምምነት ለአራት ወራት ተራዘመ

  • ቪኦኤ ዜና
የዩክሬን እህል የጫነ መርከብ፣ ኢስታንቡል፣ ቱርክ አቅራቢያ ጥቁር ባህር ላይ ሲጓዝ፣ 11/2/2022

የዩክሬን እህል የጫነ መርከብ፣ ኢስታንቡል፣ ቱርክ አቅራቢያ ጥቁር ባህር ላይ ሲጓዝ፣ 11/2/2022

የዩክሬንን እህል በጥቁር ባህር በኩል ወደውጭ ለመላክ የሚያስችለው ሥምምነት ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙን የዩክሬን እና የቱርክ ባለሥልጣናት ዛሬ ሀሙስ አስታውቀዋል፡፡

ቱርክ እና የተባበሩት መንግሥታት ባላፈው ሀምሌ በሁለቱ ወገኖች መካከል መግባባት እንዲኖር ባደረጉትጥረት፣ በሩሲያው የዩክሬን ወረራ ሳቢያ ተቋርጦ የነበረውና በድጋሚ እንዲቀጥል የተደረገው ሥምምነት የሚያበቃው በመጭው ቅዳሜ እንደነበር ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ የሥምምነቱ ጊዜ በመራዘሙ መደሰታቸውን ገልጸው “ይህ ወሳኝ የሆነ የሥርጭት መስመር ያለምንም እንከን ክፍት ሆኖ የሚቀጥልበትን መንገድ ለማረጋገጥ” የመንግሥታቱ ድርጅት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን የአቅርቦት ሥምምነቱ ጊዜ መራዘሙን አወደሰው “ሞስኮ ሥምምነቱን አላራዝምም ብትል ዓለም የማይቀበላት መሆኑን ሩሲያ በድጋሚ ስለመገንዘቧ ምልክት ነው” ብለዋል፡፡

በጥቁር ባህር ወደብ እህል እንዲተላለፍ በተደረገው ተነሳሽነት እስካሁን 11 ሚሊዮን ሚቶሪክ ቶኖች የሚደርስ የዩክሬን እህል ለማስተላለፍ የተቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው የተላከው ወደታዳጊ አገሮች መሆኑን ተመልክቷል፡፡