ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የ100ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ እንደምትሰጥ አስታወቀች

  • ቪኦኤ ዜና

በማዕከላዊ ካርኪቭ ውስጥ በተተኮሰ ጥይት የተጎዳውን ህንጻ ፍርስራሽ የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ሲያጸዳዱ መጋቢት 16/2022

ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን የ100ሚሊዮን ዶላር ወታደራዊ እርዳታ እንደምትሰጥ ዛሬ በወጣው መግለጫ አስታወቀች፡፡ ይህ የተገለጸው የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አንተኒ ብሊንክን በብራስልስ የኔቶ አባል አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ በተገኙበት ወቅት ነው፡፡

ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይህ ስብሰባ በዩክሬኑ ግጭት ላይ የሚመክር መሆኑን ተነግሯል፡፡ ብሊንክን ከቤልጅየም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሶፊ ዊለምስ ጋር ዛሬ ረቡዕ ተገናኝተው መክረዋል፡፡ ብሊንክን በኔቶ የሚኒስትሮች ስብሰባ ላይ ከመካፈላቸው በፊት ከአውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያንና የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ጋር መነጋገራቸው ተገልጿል፡፡

ብሊንከን ብራስልስ ከመድረሳቸው በፊት ትናንት ምሽት ባወጡት መግለጫ የሩሲያ ኃይሎች በቡቻና በመላው ዩክሬን የፈጸሙት ዘግኛኝ ጥቃት ዓለምን ያስደነገጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ብሊንክ አያይዘውም

“ዩክሬናውያን አገራቸውንና ነጻነታቸውን ለማስጠበቅ በቆራጥነት እየታገሉ ነው፡፡ ዩናይትድ ስቴትስና አጋሮችዋ የዩክሬን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት እንዲጠበቅ ድጋፋቸውን በመስጠት ከጎናቸው በጽናት ይቆማሉ” ብለዋል፡፡

የፔንታገን ዋና ጸኃፊ ጆን ከርቢ እርዳታው ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬን የሩሲያን ጥቃት ለመከላከል የሚያስፈልጋትና እስካሁንም ውጤታማ በሆነ መንገድ ሲከላከሉበት የቆዩትን ተጨማሪ የጦር መከላከያ መሳሪያዎችን ልክ እስከዛሬ ስትሰጥ እንደቆየቸው አሁንም የምትቀጥልበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የኔቶ ዋና ጸኃፊም ጄንስ ስቶልተንበርግ ከስብሰባው በፊት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት አጋር አገሮቹ ለዩክሬን ተጨማሪ እርዳታ ለመስጠት ቁርጠኞች ናቸው” ብለዋል፡፡

ከወታደራዊ መሳሪያውና የሳይበር ሴኩሪቲው በተጨማሪ የሰብአዊና የፋይናንስ እርዳታ እንደሚሰጡም ዋና ጸሀፊው ጨምረው ገልጸዋል፡፡ አያይዘውም “ለሩሲያ ወረራና ጣልቃ ገብነት ተጋላጭ ሊሆኑ ለሚችሉ እንደ ጆርጂያ ቦስኒያና ሄርዞጎቪና ለመሳሰሉ ሌሎቹ የኔቶ አባል አገራትም ተጨማሪ እርዳታ ለማድረግ እንወስናለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለዋል፡፡

የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሞር ኩሌባ ነገ ሀሙስ ለሚኒስትሮችን ስብሰባ ላይ ንግግር እንደሚያደርጉ በመርኃ ግብሩ ተመልክቷል፡፡

የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ እንዳስታወቀው ሩሲያ የሰብአዊ ቀውሱ እጅግ በከፋበት ማሪዮፑል ከተማ ተጨማሪ የአየር ድብደባዎች እያካሄደች መሆኑን አመልክቷል፡፡

“በከተማው ከቀሩት 160ሺ ነዋሪዎች መብራት የመገናኛ መስመር፣ መድሃኒት፣ ሙቀና ውሃ የላቸውም፡፡ የሩሲያ ኃይሎች የሰብአዊ ተደራሽነት እንዳይኖር አድርገዋል፡፡ ይህ ከተማዪቱን እየመከቱ ያሉ ሰዎች እጃቸውን እንዲሰጡ ጫና ለመስጥ ይመስላል” ሲል የሚኒስቴሩ መግለጫ አስታውቋል፡፡

የዩክሬን ፕሬዚዳን ቮሎድሚ ዘለንስኪ ትናንት ማክሰኞ ባሰሙት የቪድዮ ንግግር ምዕራባውያን መሪዎች በሩሲያ ላይ ሌላ ተጨማሪ ማዕቀብ እንዲጥሉ ጠይቀዋል፡፡