ዩክሬን ሩሲያ ማሪዮፑል ሙሉ ለሙሉ እጇን እንድትሰጥ ያቀረበችውን ጥሪ አልተቀበለችውም

የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ከኪየቭ ዩክሬን ንግግር ሲያደርጉ

ዩክሬን በሩሲያ ኃይሎች ከባድ መሳሪያ እየተደበደበች ያላቸውና የተከበበቸው ማሪዮፑል ከተማ ሙሉ ለሙሉ እጇን እንድትሰጥ ሩሲያ ያቀረበችውን ጥሪ ዛሬ ሰኞ በሰጠችው መግለጫ ውድቅ ማድረጓን አስታወቀች፡፡

የዩክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኧሪና ቨርሽቸክ የሩሲያን ጥያቄ ውድቅ ያደረጉ ሲሆን ይልቁንም ሩሲያ ሰላማዊ ዜጎች ማሪዮፑልን ለቀው የሚወጡበትን መውጫ ባር እንድትክፍት ጠይቀዋል፡፡

ሚኒስትሩ ለዩክሬን ፕራቭዳ ሲናገሩ “ትጥቅ አውርዶ እጅ ስለመስጠት ምንም ዓይነት ንግግር አይኖርም። በሩሲያ በኩል ላሉት ይህንን ከወዲሁ አሳውቀናል፡፡” ብለዋል፡፡ እንደሩሲያው የመንግሥት የዜና አገልግሎት ዘገባ የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር ለዩክሬን ጦር ትጥቃቸውን እንዲያወርዱ ዛሬ ሰኞ ቀነ ገደብ ሰጥቷል፡፡ “ይህን የማያደርጉ ከባንዶች ጋር የወገኑ ተደርገው ይወሰዳሉ” መባሉንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

የአውሮፓ የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል ሩሲያ የማሪዎፑል ድርጊት “እጅግ አስከፊ” ሲሉ ገልጸውታል፡፡ ብራስልስ ውስጥ ለተሰበሰቡት የአውሮፓ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቦሪል ሲናገሩ “ በማሪዮፑል እየሆነ ያለው መጠነ ሰፊ የጦር ወንጀል ሲሆን ያለምንም ልዩነት ያገኘውን ሁሉ እየገደለ ነው” ብለውታል፡፡

በሌላም በኩል ምሽቱን በዩክሬን ዋና ከተማ ኪዮቭ በአንድ የገበያ ማዕከል ላይ የተካሄደው ድብደባ አራት ሰዎችን መግደሉ ተነገሯል፡፡ የኪየቭ ከንቲባን ቪታሊ ክሊትሽኮቭ እስከ ከነገ ወዲያ ረቡዕ ጧት ድረስ የሰዓት ዕላፊ ማወጃቸውን አስታውቀዋል፡፡

የእንግሊዝ መከላከያ ሚኒስትር ዛሬ ሰኞ በሰሜን ኪየቭ ወጊያ እየተካሄደ ሲሆን ሩሲያውያኑ ወደ ዋና ከተማዪቱ የሚያደርጉት ግስጋሴ በ25 ኪሎ ሜትር ላይ የተገታ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ትናንት እሁድ ለሲኤንኤን አዘጋጅ ፋሪድ ዘካሪያ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ከሩሲያ ጋር ለመደርደር ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸው፣ በሚደረገው ድርድር ከሥምምነት አለመድረስ ማለት ግን የሦስተኛው ዓለም ጦርነት ይሆናል ማለት ነው” ብለዋል፡፡

በሩሲያውበኩል ድርድሩን የሚመሩት ተደራዳሪ ግን በቅርቡ በሰጡት መግለጫ “ዩክሬን የኔቶ አባል ሃገር መሆኗን በመተው ከወገንተኝነት የራቀ አካሄድ ልትከተል በመሆኑ በቅርብ ቀን ውስጥ ከስምምነት ለመድረስ እየተቃረብን ነው” ብለው መናራቸው ተመልክቷል፡፡

የተባበሩት መንግሥትታት ድርጅት ከፍተኛው የስደተኞችና ሰብአዊ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ ትናንት እሁድ ባስተላለፉት የትዊት መልዕክት የዩክሬን ጦርነት ከፍተኛ ጥፋት እያደረሰ መመሆኑን ገልጸው እስካሁን ወደ 10 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል፡፡