በአሜሪካ የወደብ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ

የወደብ ሠራተኞች የሥራ ማቆም አድማ መቱ

በአሜሪካ የወደብ ሠራተኞች ከክፍያ እና ከሌሎችም ጉዳዮች ጋራ በተያያዘ የሥራ ማቆም አድማ መተዋል። አድማው ከጥቂት ሳምንታት በላይ የሚዘልቅ ከሆነ የዋጋ ግሽበትን እና የሸቀጥ እጥረትን ሊያባብስ ይችላል ተብሏል።

45 ሺሕ ዓባላት ያሉት የወደብ ሠራተኞች ማኅበር አድማ፣ 36 ወደቦች ላይ መስተጓጎል ሊፈጥር እንደሚችል ታውቋል።

በወደቦቹ እና በሰራተኞቹ መካከል ያለው ውል ዛሬ ሌሊት ላይ እንዳበቃ ሲታወቅ፣ ድርድሩ መጠነኛ መሻሻል እያሳየ ነው ተብሏል።

ከሜይን እስከ ቴክሳስ በሚገኙ ወደቦች የሚገኙ ሠራተኞች አድማ መምታት፣ የአቅርቦት ሰንሰለቱን የሚያዛባና ከጥቂት ሳምንታት በላይ የሚቆይ ከሆነ ደግሞ የሸቀጥ እጥረትና የዋጋ ውድነት ሊያስከትል እንደሚችል ተነግሯል።

በመጪው ወር ተቀራራቢ ፉክክር የሚታይበት ምርጫ ሊደረግ ዕቅድ በተያዘበት ወቅት የተጠራው አድማ፣ በመራጮች ላይ ተጽእኖ የሚያሳደር ከሆነ፣ የምርጫው አንዱ ጉዳይ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።