ተመራጩ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ ለአዲሱ የዋይት ሀውስ አስተዳደራቸው ቁልፍ ቦታዎች የሚሰጡትን ሹመት ለማመቻቸት ከወዲሁ በፍጥነት እየተንቀሳቀሱ ሲሆን የመረጧቸውን ሰዎች በቀናት ውስጥ ሊሰይሙ እንደሚችሉ ተነገረ።
ትረምፕ በማክሰኞው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስን ወሳኝ በሆነ ድል ከረቱ በኋላ በፍሎሪዳ የባህር ዳርቻው በሚገኘው የ ማር-አ-ላጎ መኖሪያ ቤታቸው ከረዳቶች ጋር እየመከሩ መሆኑ ተነገሯል፡፡
ከምርጫው በፊትም ቢሆን የሽግግር አመቻች ኃላፊው ሃዋርድ ሉትኒክ እና ሊንዳ ማክማሆን በዋይት ሀውስ ወይም በመንግስት ካቢኔ-ደረጃ የተመደቡ ወይም መምሪያዎችን እና ሌሎች ተቋማትን ለመምራት ከታጩ አንዳንድ እጩ ተወዳዳሪዎች ጋር ተገናኝተዋል።
የትረምፕ ረዳቶች ባለፉት አራት ዓመታት በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የወጡትን ፖሊሲዎች ለማስቆም፣ ትረምፕ ሥራ በሚጀምሩበት የመጀመሪያ ቀን ፣ እኤአ ጥር 20 እንዲፈርሙ ረጅም የስራ አስፈፃሚ ትዕዛዞችን እና የቁጥጥር ለውጦችን አዘጋጅተዋል ።
እ.ኤ.አ. በ2020 ምርጫ ትረምፕን ያሸነፉት እና በሰኔ ወር ከትረምፕ ጋር በተደረገ ክርክር ባሳዩት ደካማ አፈጻጸም ከውድድሩ የወጡት ባይደን፣ ወደ ትረምፕ የሚደረገውን ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡
ባይደን በመጪዎቹ ቀናት ተመራጩን ፕሬዝዳንት ወደ ዋይት ሀውስ ለጉብኝት የጋበዙ ሲሆን ትላንት ረቡዕ በስልክ የ “እንኳን ደስ አልዎት መልእክት” አስተላልፈዋል።
ባይደን ምርጫውን አስመልክቶ ዛሬ ሀሙስ በዋይት ሀውስ ሮስ ጋርደን ንግግር አሰምተዋል፡፡
ባይደን ትላንት ረቡዕ ሃሪስ “በጣም ጥሩ አጋር እና በቅንነት፣ ድፍረት እና ባህሪ የተሞላች የህዝብ አገልጋይ ነች።” ሲሉ በምርጫው ዘመቻ ያደረጉትን ሥራ አድንቀዋል፡፡