የሩሲያ ያየር ድብደባዎች፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሦሪያ ሲቪሎችን መግደላቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች በከፍተኛ ደረጃ አዕምሮን የሚረብሹ ናቸው ስትል ዩናይትድ ስቴትስ አስታወቀች።
ዋሽንግተን ዲሲ —
የሩሲያ ያየር ድብደባዎች፥ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሦሪያ ሲቪሎችን መግደላቸውን የሚገልጹ ዘገባዎች በከፍተኛ ደረጃ አዕምሮን የሚረብሹ ናቸው፥ ባላጭ ሕዝቦች ላይ የሚደርሡ ጥቃቶችም ለሃገሪቱ ችግር የፖለቲካ መፍትሄ ለማምጣት የተያዙ ጥረቶችንም ያበላሻሉ ስትል ዩናይትድ ስቴትስ አስታወቀች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማርክ ቶነር (Mark Toner) ይህንኑ አስመልክተው ትላንት ሲናገሩ፥ በመጭው ወር እንዲደረግ ከታቀደው የሰላም ንግግር አስቀድሞ ትኩረቱ፥ የፖለቲካ ሂደቱን መግፋት ነው፥ በዚህም በሦሪያ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ፥ በትምምን ግንባታ እርምጃዎች ላይ መሥራት ያስፈልጋቸዋል ብለዋል።
የሩሲያ ያየር ድብደባ ሲቪሎችን ዒላማ ማድረጉን ያስታወቁት፥ የሰብዓዊ መብት ተከራካሪ ቡድኖች ናቸው። ምዕራባውያን መንግሥታትም፥ የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ፥ በእስላማዊ መንግሥቱ ሚሊሽያዎች ላይ ከማነጣጠር ይልቅ፥ ፕሬዘዳንቱን ባሽር አል-አሳድን (Bashar Al-Assad) እያጠናከረ ነው ሲሉ ይተቻሉ።