ስዊዲን 32ኛው የኔቶ አባል በመሆን የቃል ኪዳን ድርጅቱን ትናንት ሐሙስ ተቀላቅላለች፡፡ ባለሥልጣናት እንደሚሉት ውሳኔው የተሳለጠው ሩሲያ ዩክሬንን በመውረሯ ምክንያት ነው። በተጨማሪም የቃል ኪዳን ድርጅቱ ዓባል አገራት ከፍተኛ ወታደራዊ ልምምድ በሚያደርጉበት ወቅት የመጣ ውሳኔ መሆኑ ተገጿል።
የስዊዲኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኡልፍ ክሪስተሸን ትናንት የአሜሪካው ፕሬዝደንት በኮንግረስ ባደረጉት “ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን” ንግግር ላይ በቀዳማዊ እመቤት ጂል ባይደን ጋባዥነት ተገኝተው ነበር።
ከፑቲን ወረራ በፊት ኔይቶን መቀላቀል የሚሹት ስዊዲናውያን ቁጥር ከአንድ ሦስተኛ ያነሱ እንደነበር ያወሱት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ ከወረራው በኋላ ግን ሦስት አራተኛ የሚሆነው የስዊዲን ሕዝብ የቃል ኪዳን ድርጅቱን መቀላቀልን ደግፏል ብለዋል።
በሩሲያ ወረራ ምክንያት፣ አውሮፓ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ አስጊ ሁኔታ ውስጥ የገባችበት ሁኔታ እንደተፈጠረ የገለጹት የስዊዲኑ ጠቅላይ ሚኒስትር፣ አገራቸው በምድር፣ በአየር እና በባሕር አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል አቅም እንዳላት ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ቮሎዲሚር ዜሌኒስኪ ስዊዲን ኔቶን የመቀላቀሏን ዜና በደስታ ተቀብለዋል።