በዩናይትድ ስቴትስ ሰሜናዊ ምሥራቅ ሜይን ግዛት ውስጥ፣ ትላንት ረቡዕ ምሽት፣ ቢያንስ 16 ሰዎችን ገድሎ በርካቶችን አቁስሏል የተባለውን ተጠርጣሪ ለመያዝ የሚደረገው ፍለጋ፣ አሁንም እንደቀጠለ መኾኑን፣ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ሮበርት ካርድ የተባለው ተጠርጣሪ፣ በወትድርና የሠለጠነ የጦር መሣሪያ አስተማሪ ሲኾን፣ በቅርቡ በአእምሮ ጤና ሕክምና ተቋም እንደታየ፣ አሶሼዬትድ ፕሬስ የተመለከተው የፖሊስ ሰነድ ያመለክታል፡፡
የሉዊስተን ፖሊስ በፌስቡክ ገጹ እንዳረጋገጠው፣ ካርድ በጥቃቱ ተሳትፏል፡፡ “አሁንም የታጠቀ እና አደገኛ ተደርጎ ሊወሰድ ይገባል፤” ብሏል፡፡
ካርድ፣ ረቡዕ ምሽት፣ በሉዊስተን አንድ መጠጥ ቤት ውስጥ በሚገኝ የቦውሊንግ መጫወቻ ስፍራ በከፈተው ድንገተኛ ተኩስ፣ የክፍለ ግዛቷን ሁለተኛ ትልቅ ከተማ ማናወጡ ተጠቅሷል፡፡
በደረሰው ጥቃት በርካታ ሰዎች እንደቆሰሉ፣ ሁለት የሕግ አስከባሪ ባለሥልጣናት ለአሶሺዬትድ ፕሬስ ተናግረዋል፡፡
የሜይን ፖሊስ መምሪያ ኮሚሽነር ማይክ ሶስቸክ፣ “በሜይን ግዛት ዙሪያ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የፖሊስ መኰንኖች ይህን ጉዳይ ለመመርመር እየሠሩ ነው፤” ሲሉ አስታውቀዋል፡፡
የተጠርጣሪው እንደኾነ የተገመተ ተሽከርካሪም፣ ረቡዕ ምሽት ሜይን ሊስቦን ውስጥ እንደተገኘ፣ ኮሚሽነሩ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
“የታጠቀ እና አደገኛ ነው፤” ከተባለው ተጠርጣሪ፣ የከተማዪቱ ነዋሪዎች ራሳቸውን እንዲጠብቁም፣ ኮሚሽነሩ መክረዋል፡፡
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ ከክፍለ ግዛቷ አገረ ገዥ ጃኔት ሚልስ እና ከግዛቱ የሕዝብ እንደራሴዎች ጋራ በስልክ ተነጋግረዋል፡፡
በአሠቃቂ ጥቃቱ የፌደራል መንግሥቱ ሙሉ ድጋፍ እንደሚያድረግ፣ ፕሬዚዳንቱ ቃል እንደገቡ፣ ዋይት ሐውስ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡