በካንሳስ ሲቲ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሰው ሲሞት 22 ቆሰሉ

  • ቪኦኤ ዜና

ተኩሱን ሸሽተው የሚሮጡ ታዳሚዎች ዩናትይትድ ስቴትስ ሚዙሪ ክፍለ ግዛት ካንሳስ ሲቲ

ዩናትይትድ ስቴትስ ሚዙሪ ክፍለ ግዛት ካንሳስ ሲቲ ውስጥ ትንናት ረቡዕ የከተማው የእግር ኳስ ቡድንና ደጋፊዎች ባደርጉት ሰልፍ ላይ በተከፈተ ተኩስ አንድ ሰው ሲገደል፣ ሕጻናትን ጨምሮ ቢያንስ 22 ሰዎች መቁሰላቸውን ባለስልጣናት አስታወቁ፡፡

ጉዳቱ የደረሰው፣ ባለፈው እሁድ ሱፐር ቦውል አሸናፊ የሆነውን የካንሳስ ሲቲ ቺፍስ፣ ደጋፊዎቹ በተለያዩ ዝግጅቶች ለማክበርና ቡድኑን ለመቀበል አደባባይ በወጡበት ሥነ ስርዓት መጠናቀቂያ ላይ መሆኑ ተመልክቷል፡፡

በከተማው ታዋቂ የሆነው የኬኬፍአይ(KKFI) ሬዲዮ ጣቢያ ሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) ሊሳ ሎፔዝ መገደሏን የካንሳስ ሲቲ ፖሊስ አዛዥ ስቴሲ ግሬቭስ አስታወቀዋል፡፡

ከተኩስ ጥቃቱ ጋር በተገናኘ የተያዙ ሰዎች መኖራቸውንም የገለጹት አዛዡ፣ “በቁጥጥር ሥር የሚገኙ ሶስት ሰዎች ያሉን ሲሆን በምርመራ ላይ ይገኛሉ፡፡ ከሶስቱ አንደኛው ግለሰብ ደጋፊዎቹ ፖሊስን ሲረዱ በሚያሳየው ቪዲዮ ላይ ከሚታዩት ውስጥ አንዱ መሆኑን ለማረጋገጥ እየሠራን ነው" ብለዋል፡፡

ፖሊሶች በተጨናነቀ ህዝብ መካከል ሲሮጡ እንዲሁም ሰዎች ራሳቸውን ከአደጋው ለመከለል ሲሯሯጡ የሚያሳይ አስደንጋጭ ቪዲዮ በማህበራዊ መዲያ ተጠቃሚዎች ተሰራጭቷል፡፡

ተኩስ በተከፈተበት ወቅት፣ ተጫዋቾቹ እና አሰልጣኞች በአውቶቡሶች ሆነው ወደ አሮውሄድ ስታዲየም ለመመለስ በጉዞ ላይ እንደነበሩ የቺፍስ ቡድን ሥራ አስኪያጅ ተናግረዋል።

ፖሊስ በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ሰዎችም ሆነ የተኩስ ጥቃቱ ምክንያት ምን እንደሆነ ወዲያውኑ አልገለጸም።

የካንሳስ ሲቲ ከንቲባ ኩዊንተን ሉከስ “ዛሬ በሰልፉ ላይ ተሳታፊ ለነበሩት ሁሉ እጅግ አሳዛኝ ዕለት ነው” ብለዋል፡፡

ካንሳስ ሲቲ የመሣሪያ ጥቃት በተደጋጋሚ ሲፈጸምባት ይስተዋላል። እ.አ.አ በ2020 ዓ/ም፣ የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ሚኒስትር የጥቃት ወንጀሎችን ለመቆጣጠር ኢላማ ካደረጋቸው ዘጠኝ ከተሞች መካከል አንዷ ነበረች። እኤአ በ2023 በከተማዋ 182 ግድያዎች ተመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህ አብዛኞቹ በሽጉጥ የተፈጸሙ መሆናቸው ተጠቅሷል፡፡