በዩናይትድ ስቴትስ የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ክላውዲን ጌይ ከመጭው ማክሰኞ ጀምሮ ከኃላፊነታቸው እንደሚለቁ ተናገሩ፡፡
ፕሬዝዳንትዋ ይህን ያስታወቁት የእስራኤል ሐማስ ጦርነትን ተከትሎ በዩኒቨርስቲው ውስጥ ታይቷል በተባለው ጸረ ሴማዊነት እና ስምና ምንጭ ሳይጠይቅሱ የሰውን ሥራ ያለፈቃድ እንደራሳቸው አድርገው ተጠቅመዋል በሚል ክስ (plagiarism) ቃላቸውን እንዲሰጡ በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ፊት ከቀረቡ በኋላ ነው፡፡
ጌይ እኤአ ታህሳስ 5፣ 2023 በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው በሰጡት አስተያየት በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ከሚገኙ የአይሁድ ማህበረሰብ እና ከአንዳንድ የምክር ቤት አባላት ከኃላፊነታቸው እንዲለቁ ግፊት ገጥሟቸው ነበር፡፡
ፕሬዝዳንቷ ስምና ምንጭ ሳይጠይቅሱ የሰውን ሥራ ያለፈቃድ በመውሰድ እንደራሳቸው አድርገው በጥናታዊ ሥራቸው ተጠቅመዋል በሚል በርካታ ክሶችም ቀርበውባቸዋል፡፡
የፕሬዝዳንትዋ ከኃላፊነት መነሳት ከደጋፊዎቻቸው እና ተቺዎቻቸው ዘንድ የተለያዩ አስተያየቶች አስተናግዷል፡፡
ጌይ ለሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ አስተዳዳሪ አካል በፃፉት ደብዳቤ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ ያደረጉት ውሳኔ "ከቃላት በላይ አስቸጋሪ ነበር" ብለዋል፡፡
የሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ለህብረተሰቡ በላከው ኢሜል እንዳስታወቀው የዩኒቨስቲው ማህበረሰብ አባላት የጌይን ከኃላፊነት መልቀቅ “በሀዘን” እንደተቀበሉት ተናግረዋል፡፡
ጌይን ጨምሮ ፣ የቀድሞ የፔንስልቬንያ ፕሬዝደንት ሊዝ ማጊል፣ እና የማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ተቋም ፕሬዝዳንት ሳሊ ኮርንብሉት፣ እኤአ ታህሳስ 5፣ 2023 በዩናይትድ ስቴትስ ምክር ቤት ኮሚቴ ፊት ቀርበው የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት ከተቀሰቀሰበት እኤአ ጥቅምት ወር ወዲህ በኮሌጆቹ ግቢዎች ጨምሯል ስለተባለው ፀረ-ሴማዊነት ጉዳይ የምስክርነት ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡