የአሜሪካ የግብርና ኢንዱስትሪ ባለቤቶች ትራምፕ ሠራተኞቻቸውን ከሀገር እንዳያባርሩ ጠየቁ

  • ቪኦኤ ዜና

የሜክሲኮ ስደተኛው በመኸር ወቅት በዌልስ ሃይቅ፣ ፍሎሪዳ በሚገኝ የእንጆሪ እርሻ በሥራ ላይ እአአ መጋቢት 31/2020

የዩናይትድ ስቴትስ የግብርና ኢንዱስትሪ ተቋማት፣ ተመራጩ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በህገወጥ መንገድ የገቡ ስደተኞችን ለማባረር የገቡት ቃል በግብርና ዘርፉ በተሰማሩ ሠራተኞች ላይ ተፈፃሚ እንዳይሆን ጠየቁ። ተቋማቱ ይህን የጠየቁት፣ ውሳኔው ህጋዊ ፈቃድ በሌላቸው ስደተኞች ሥራ ላይ በከፍተኛ ደረጃ የሚመረኮዘውን የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ሊያናጋው እንደሚችል በመግለፅ ነው።

ከግብርና ኢንዱስትሪ ባለሐብቶች ሠራተኞች እና የአሜሪካን ድንበር እንዲያስተዳድሩ ትረምፕ ከአጯቸው ቶም ሆማን ጋር በተደረጉ ቃለ ምልልሶች መሠረት፣ የትረምፕ ባለስልጣናት ከመባረር ነፃ የሚሆን ህገወጥ ስደተኛ እንደሚኖር አልጠቀሱም።

የሀገሪቱ የሠራተኛ እና ግብርና ሚኒስቴር መሥሪያ ያ ቤቶች መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ አሜሪካ ውስጥ በእርሻ ስራ ከተሰማሩ ወደ 2 ሚሊየን የሚጠጉ ሠራተኞች ውስጥ ግማሽ ያክሉ ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የላቸውም። አብዛኞቹ የወተት እና የሥጋ ማሸጊያ ፋብሪካዎች ሠራተኞችም ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ስደተኞች ናቸው።

ሪፐብሊካኑ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ትረምፕ ወደዋይት ኃውስ ለመመለስ ባደረጉት ዘመቻ፣ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ የገቡ በሚሊየን የሚቆጠሩ ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው እንደሚመልሱ ቃል ገብተዋል። ተቺዎች በበኩላቸው ተግባራዊ ለማድረግ ፈታኝ የሆነው ውሳኔ ቤተሰቦችን ሊለያይ እና የአሜሪካ የንግድ ተቋማትን እንደሚያናጋ አመልክተዋል።

ሆማን በቅድሚያ ወንጀለኞች እና ከሀገር እንዲወጡ በፍርድ ቤት የታዘዙ እንደሚባረሩ ገልጸው፣ ሆኖም ያለህጋዊ ፈቃድ አሜሪካ ያለ እና የማባረር ውሳኔው የማይመለከተው ስደተኛ ግን አይኖርም ብለዋል።

በሚቺጋን ስቴት ዩንቨርስቲ የምግብ ኢኮኖሚክስ እና ፖሊሲ መምህር የሆኑት ዴቪድ ኦርቴጋ፣ ሠራተኞችን በጅምላ ማባረር የምግብ አቅርቦት ሠንሰለቱን ከማናጋቱ በተጨማሪ ሸማቾች ለሸቀጦች የሚያወጡትን ዋጋ ከፍ እንደሚያደርግ አመልክተው፣ "የግብርና ሠራተኞቹ የአገሬው ተወላጅ አሜሪካውያን ሊሠሩ የማይችሉትን ወይም የማይፈልጉትን ሥራ በመሥራት ወሳኝ አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ናቸው" ሲሉ አብራርተዋል።

የትረምፕ ሽግግር ኮሚቴ ቃል አቀባይ ካሮሊን ሌቪት የግብርና ዘርፍ ባለቤቶቹን ስጋት አስመልክቶ ከሮይተርስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም።

ትረምፕ በመጀመሪያው የሥልጣን ዘመናቸው፣ በምግብ ዘርፉ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞችን እንደማያባርሩ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም፣ አስተዳደራቸው ሚሲሲፒ ክፍለ ግዛት የሚገኙ የዶሮ እርባታ ፋብሪካዎችን እና ኔብራስካ ውስጥ ያሉ የምግብ ማምረቻዎች ውስጥ ድንገት ደራሽ ፍተሻ በማድረግ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸው ሠራተኞችን በጅምላ አስሯል።