ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት በአፍጋኒስታን ካቡል የአየር ማረፊያ አካባቢ ጥቃት ሊያደርስ ይችላል ተብሎ በተጠረጠረ መኪና ላይ ጥቃት አድርሳለች።
የማዕከላዊ እዙ ቃል አቀባይ ካፒቴን ቢል ኧርባን እንደተናገሩት ዩናይትድ ስቴትስ የራስ መከላከል ጥቃቱን የፈፀመችው አይሲስ ኬ የተሰኘው ቡድን በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ ግልፅ የሆነ ጥቃት ሊያደርስ መሆኑ ስለተደረሰበት ነው ብለዋል።
ፕሬዚዳን ጆ ባይደን ከጥቃቱ አስቀድመው ትናንት በሰጡት መግለጫ "በሚቀጥሉት 24 እና 26 ሰዓታት ውስጥ በአፍጋኒስታን ካቡል ፣ሌላ ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀው ነበር። ከሰዓታት በኋላም በካቡል ያለው የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲም ጥቃት ሊፈጸም እንደሆነ ከታመነ ምንጭ በማረጋገጡ በአውሮፕላን ማረፊያው የሚገኙ ዜጎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቋል፡፡
አይ ሲስ ኬ የተባለው ቡድን ባለፈው ሳምንት ሀሙስ 170 አፍጋኖችን እና 13 የዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮችን ለገደለው አጥፍቶ ጠፊ የቦምብ ጥቃት ሀላፊነቱን መውሰዱ ይታወሳል። ለጥቃቱ አጸፋውን ለመስጠት በማግስቱ አርብ የዩናይትድ ስቴትስ ባካሄደችው የአየር ድብደባ የአሸባሪው ቡድን ሁለት ዋና ዋና አባላት መገደላቸውም ተዘግቧል።
ፕሬዚዳንት ባይደንና ባለቤታቸው ጂል በቦምብ ጥቃቱ ህይወታቸውን ያጡትን 13 አሜሪካውያንን አስክሬን ዴላዌር በሚገኘው የአየር ኃይል ሰፈር ተቀብለው አክብሮታቸውን ገልጸዋል፡፡ ከሟቾቹ ቤተሰቦች ጋርም ተገናኝተዋል፡፡