አሜሪካ ኢትዮጵያ ለምርጫው ሜዳውን ማመቻቸት ይኖርባታል አለች

ዩናይትድ ስቴትስ በኢትዮጵያ የሚካሄደውን የዴሞክራሲ ሂደት አጥብቃ የምትደግፍ ሲሆን፣ እኤአ ሰኔ 5 የሚካሄደው ምርጫ “ነጻ ፍትሃዊና ተአማኒ ሊሆን የሚችለው ለመራጮች የተመቻቸ ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ መሆኑን" አስታውቃለች፡፡

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ትናንት የተሰጠው መግለጫ የወጣው በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ያለው ሰብአዊ ቀውስና ግጭት እየተካሄደ ባለበት ሁኔታ ውስጥ ነው፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ምኒስቴር አንተኒ ብሊንከንም ኢትዮጵያና ኤርትራ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ “አሁኑኑ፣ ሙሉ ለሙሉ፣ ሊረጋገጥ በሚችል መልኩ” ለቀው እንዲወጡ ከዚህ ቀደም በሰጡት መግለጫ ብርቱ ግፊት አድርገዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ባለፈው መጋቢት ወር ኤርትራ ከትግራይ ክልል ኃይሎችዋን ለማስወጣት መስማማቷን ገልጻ ነበር፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይም ወደ ኤርትራ በማምራት ከፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ተገናኝተው ኤርትራ ለቃ እንደምትወጣ ያረጋገጠችላቸው መሆኑን ያስታወቁ ቢሆንም የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ግን እስከዛሬ ድረስ ኤርትራ ለቃ ስለመውጣቷ ምንም ማረጋጋጫ አለመኖሩን ተናግረዋል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

አሜሪካ ኢትዮጵያ ለምርጫው ሜዳውን ማመቻቸት ይኖርባታል አለች

መራጮች ምዝገባ ላይ ችግር በመኖሩ ፣ ኢትዮጵያ እኤአ ሰኔ 5 ለምታደርገው ጠቅላላ ምርጫ ለመዘጋጀት እየተጣጣረች ነው፡፡ ካለፈው ነሀሴ ጀምሮም በኮቪድ 19 የተነሳ ጠቅላላው ምርጫ ሳይካሄድ መዘግየቱ ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባና ድሬዳዋ አስተዳደሮችም ምርጫውን ለማካሄድ ያቀዱት እኤአ ሰኔ 12 መሆኑን ተመልክቷል፡፡

የውጭ ጉዳይ ምኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት ሰኞ በሰጡት መግለጫቸው ላይ ፣ ምርጫው የሚካሄደበት ምቹ ሁኔታ ከተሟላ የኢትዮጵያ መንግሥት የመሰብሰብና የንግግር ነጻነትን መፍቀድ፣ የፖለቲካ ተሳትፎንና እንዲሁም ሰዎች ኢንተርኔትና የመረጃ አገልግሎትን እንዲያገኙ ማድረግ ይኖርበታል” ብለዋል፡፡

አያይዘውም “የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሁከትና ጥቃትን ማበረታት እንደሌለባቸው እናውቃለን፣ የጸጥታ አስከባሪ ኃይሎችም የኃይል እምርጃዎችና መውሰድና በተቃዋሚዎች ላይ የማስፈራሪያ ስልቶችን መጠቀም የለባቸውም” ብለዋል፡፡ ቃል አቀባዩ ከቪኦኤ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት መልስ

“ከዓለም አቀፍ አጋሮቻችን ጋር ምርጫውን ተከትሎ ሁከትና ጥቃትን ለማስወገድ በማህበረሰቡ መካከል መነጋገር እንዲኖር እናበረታታለን፡፡” ብለዋል፡፡

ይሁን እንጂ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫው ሊካሄድ ይችላል ብሎ ስለማመን አለማመኑ የገለጸው ነገር የለም፡፡

የኢትዮጵያ የቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር የነበሩት ዴቪድ ሽን ለቪኦኤ እንደተናገሩት "በትግራይ ክልል ምርጫውን ለማካሄድ አይቻልም፡፡ ከትግራይም ውጭ ኢትዮጵያ ውስጥ “ የሰኔ አምስቱ ምርጫ የሚያዋጣ ስለመሆኑ የሚያሳስቡ አንዳንድ ተጨባጭ ስጋቶች አሉ፡፡” ብለዋል፡፡

የሚታዩ አለመረጋጋቶችና በውጭ ታዛቢዎች ላይ የተጣሉ ገደቦች የምርጫው ሂደት ላይ አንዳንድ ጥያቄዎችን እንዲያነሱ አድርገዋል፡፡ እኤአ ግንቦት 3 የአውሮፓ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ጆሴፍ ቦረል በሰጡት መግለጫ “ቁልፍ በሆኑ ጉዳዮች ላይ” ስምምነት ባለመደረሱና “አስፈላጊ ሁኔታዎች ያልተሟሉ በመሆናቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚሄዱት የምርጫ ታዛቢዎችን የመላኩ እቅድ የተሰረዘ መሆኑን” አስታወቀው ነበር፡፡

ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ በዛሬው እለት በሰጡት መግለጫ የአውሮፓ ህብረት 6 ታዛቢዎችን ለመላክ መስማማቱን አስታውቀዋል፡፡

ትናንት ሰኞ የዩናይትድ ሴትትስ ከሁለቱም የዴሞክራትና የሪፐብሊካን ፓርቲ ወገኖች የሆኑት የህዝብ ተወካዮች ምክርቤት አባላት ደግሞ በጋራ ባወጡት መግለጫ ትግራይ ውስጥ ያሉ የኤርትራ ኃይሎች ጉዳይ አሁንም እጅግ ያሳሰባቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዩናይትድ ስቴትስ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሊቀመንበር ማይክ መካውል ስለዚሁ ሲናገሩ

፣“ግጭትና ጠበኝነትን አስወግዶ ሁሉን አሳታፊ ወደ ሆነው የፖለቲካ ንግግር ሊያመጣ የሚችለው ወታደራዊ እርምጃ አይደለም፡፡ አሁንም ትግራይ ውስጥ ያሉት የኤርትራ ወታደሮች በክልሉ የሚፈጽሙ የሰአብዊ መብት ጥሰት ግጭቱን ለማስወገድ ትልቁ እንቅፋት እንደሆነ ቀጥሏል" ብለዋል፡፡፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ መንግሥት፣ በትግራይ የሚደረገውን ግፍ እንዲቆም እንዲያደርጉ ጫና ለማሳደር፣ ከሰአብአዊ ድጋፍ ውጭ ያለውን እርዳታ ማቋረጧን የምትቀጥልበት መሆኑም ተመልክቷል፡፡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ግን ለአገሪቱ የሚሰጠውን የሰብአዊ እርዳታ መሰጠቱን የሚቀጥልበት መሆኑ አስታውቋል፡፡፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ፕራይስ ይህንኑ ሲገልጹ

“ ለኢትዮጵያ እርዳታውን ለመስጠት ስናስብ፣ በዚያ አስቸጋሪ መከራ ውስጥ በሚገኘው የትግራይ ህዝብ ላይ ሌላ ተጨማሪ ጫና የሚያሳድር ነገር ማድረግ አንፈልግም፡፡ እንዲያውም ወደፊት የበለጠ ልንግዛቸው የምንችልበት መንገድ መኖሩን ማረጋገጥ እንፈልጋለን፡፡" ብለዋል፡፡

በቅርቡ ለንደን ውስጥ የተገናኙት የቡድን 7 የበለጸጉ አገር ውጭ ጉዳይ ሚንስትሮች ከተነጋገሩባቸው ጉዳዮች አንዱ የትግራይ ጉዳይ ነበር፡፡

የውጭ ጉዳይ ምኒስትሮቹ ባወጡት የጋራ መግለጫ “ሁሉም ወገኖች ግጭቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ፣ የሰላማዊ ዜጎች ደህንነት መጠበቁን እንዲያረጋግጡ፣ ዓለም አቀፍን የሰአብአዊ መብት እና ዓለም አቀፍ ህግጋትን እንዲጠብቁ የሚዲያ ነጻነት እና ተደራሽነት እንዲኖር፣ አስገድዶ መድፈረና ጥቃትን ጨምሮ በሰ አብዊ መብት ጥሰትና ጥቃት የፈጸሙት ሁሉ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማሳሰባቸው የሚታወስ ነው፡፡

(የቪኦኤ ዘጋቢ ኒክ ቺንግ ካጠናቀረችው ዘገባ የተወሰደ፡፡)