አሜሪካውያን የምርጫውን ውጤት እየተጠባበቁ ነው

ፎቶ ፋይል፦ የድምፅ ቆጠራ በኦሬጋን

አሜሪካውያን በአፎካካሪና አሻሚዎቹ ግዛቶች አሁንም ለይቶ ያልታወቀውን የፕሬዛዳንታዊ ምርጫ ውጤት እየተጠባበቁ ነው፡፡ አሁን በሥልጣን ላይ ያሉት ሪፐብሊካኑ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለሚቀጥሉት አራት ዓመታት በሥራ አስፈጻሚነት ይቀጥሉ እንደሆነ፣ ወይም ዴሞክራቱ ተፎካካሪያቸው የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የሚተኳቸው ስለመሆኑ የታወቀ ነገር የለም ስትል ከዋይት ሐውስ የቪኦኤ ዘጋቢ ፓትሲ ውዳክስዋራ ዘገባ አጠናቅራለች፡፡

ትናንት ማክሰኞ፣ ከተፎካካሪዎቹ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ እና ከቀድሞ ም/ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን፣ አሸናፊው እንደሚለይ ተስፋ በማድረግ፣ በዋሽንግተን ዲሲና ፍሎሪዳ ማያሚ የሚገኙ ደጋፊዎች ፤ በየጎዳናዎች ላይ ደስታቸውን ለመግለጽ ተዘጋጅተው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ትራምፕም ሆነ ባይደን አንዳቸውም ለፕሬዚዳንትነት፣ ከሚያበቃቸው ከ538 የውክልና ድምጾች ውስጥ፣ ማግኘት የሚገባቸውን ቢያንስ የ270 ድምጽ እንኳ ሊያገኙ አልተቻላቸውም፡፡ የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ውጤት የሚወሰነው፣ አብላጫውን የህዝብ ድምጽ ባሸነፈ ሳይሆን፣ በግዛቶች መካከል የተደለደለውን የውክልና ድምጽ ባሸነፈ ነው፡፡ በጆርጅ ሜሰን ዩንቨርስቲ የፖለቲካ የአሜሪካን ፖለቲካ የሚያስተምሩት ጀርሚ ሜየር እንዲህ ይላሉ

"እኔ እኔ እንደሚመስለኝ ሁለቱም እጩዎች 50 50 ከመቶ እድል ያላቸው ይመስለኛል፡፡ በጣም የሚገርመው ሁሉ ነገር ተመልሶ፣ በ2016ቱ ምርጫ ጊዜ እንደነበረው መሆኑ ነው፡፡ አሁንም ተመልሶ በእነዚያው ሶስቱ ክፍለ ግዛቶች ውስካንሰን ሚችጋንና ፐንሰልቬያ ላይ ነው ያረፈው፡፡

ውስካንሰን ሚችጋን እና ፐንሰልቬንያ በተለምዶ የዴሞክራቶች ግዛቶች የነበሩ ሲሆን በ2016ቱ ምርጫ ትራምፕ አሸንፈዋቸዋል፡፡ ሁለቱም እጩዎች፣ በተለይ ወደ መጨረሻው ላይ፣ በእነዚህ አካባቢዎች በርካታ የምርጫ ዘመቻዎችን አካሂደዋል፡፡ እስካሁን ተረጋግጦ የታወቀ ውጤት ግን የለም፡፡ ጆ ባይደ በትናንትናው ምሽት ቀደም ብለው ባሰሙት ንግግር እንዲህ ብለዋል፡፡

“ጎበዝ እምነታችሁን አጠንክራችሁ ያዙ፡፡ ይህን እናሸነፋለን፡፡ አመሰግናለሁ! አመሰግናለሁ!”

ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ፣ ፕሬዚዳንት ትራምፕ በሰጡት የቲውት ምላሽና፣ ቲውተር “አሳሳች ነው” የሚል ምልክት ባኖረበት አስተያያታቸው፣ ዴሞክራቶቹ ምርጫውን ሊሰርቁት ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ቆየት ብለው ከዋይት ሐውስ ባሰሙት ንግግር ደግሞ፣ ይህን ብለዋል

“ይህ በጣም የሚያሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ለኔ ይህ በጣም አሳዛኝ ጊዜ ነው፡፡ እኔ እስከሚገባኝ ድረስ ይህን ምርጫ አሸንፈናል፡፡”

ምንም እንኳ፣ ፕሬዚዳንት ትራንፕ ማሸነፋቸውን ቢገልጹም፣ የምርጫ ድምጾች ቆጠራው የሚቀጥል ሲሆን፣ አሸናፊውን ለማወቅ ምናልባት ቀናትን ሊወስድ እንደሚችል ተገምቷል፡፡ ከአተርቤን ዩኒቨርስቲ ላትሪስ ዋሽንግተን እንዲህ ይላሉ

በወረርሽኙ ሳቢያ ብዙዎቹ መራጮች ድምጽ የሰጡት በአካል ሳይሆን አስቀድመው ወረቀት ላይ ሞልተው በላኩት ድምጽ ነው፡፡ ያ ዓይነቱ የድምጽ አሰጠጣ ደግሞ በብዛት በመጨመሩ ቆጠራውን በጥቂቱ ሊያጓትተው ይችላል፡፡

ምንም እንኳ፣ ሁከት የተሞላበትና ከፋፋይ የነበረው የምርጫ ዘመቻን ተከትሎ፣ ችግር ሊከተል ይችላል በሚል፣ በአንዳንድ የምርጫ ጣቢዎች፣ ከወትሮው በተለየ መልኩ፣ በርከት ያሉ ፖሊሶች የታዩ ቢሆንም፣ አሜሪካውያን፣ ድምጻቸውን የሰጡት፣ አንጻራዊ በሆነ መልኩ፣ በተረጋጋና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ነው፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያድምጡ፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

አሜሪካውያን የምርጫውን ውጤት እየተጠባበቁ ነው