የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል ትናንት ሰኞ የመን ውስጥ ባደረሰው ጥቃት ሰባት ሚሳይሎች እና ሦስት ሰው አልባ አውሮፕላኖች መደምሰሱን አስታወቀ። ጥቃቱን ያደረሰው በንግድ መርከቦች እና በዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል ላይ ስጋት የደቀኑት ሁቲ አማጽያን በሚቆጣጠሩት የየመን አካባቢ መሆኑን አመልክቷል።
ኢራን የምትደግፋቸው ሁቲ ታጣቂዎች ካለፈው ኅዳር ጀምረው በቀይ ባሕር አካባቢ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ። ምክንያታቸውም እስራኤል ጋዛ ውስጥ ከሀማስ ጋር በምታካሂደው ጦርነት "ከፍልስጤማዊያን ጎን መቆማችንን ለማሳየት ነው" ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የጦር ኃይል ማዕከላዊ ዕዝ በ"ኤክስ" ገጹ ላይ ባወጣው መግለጫ " ኃይሎቻችን በሁቲዎቹ ቁጥጥር ሥር ባለው አካባቢ በወሰዱት ራስን የመከላከል እርምጃ ጸረ መርከብ ሚሳይሎች እና ድሮኖች እንዲሁም ሦስት የጦር መሣሪያ ማከማቻዎች ደምስሰዋል" ሲል አመልክቷል።
መሣሪያዎቹ በንግድ መርከቦች እና በዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል መርከቦች ላይ አደጋ በመደቀናቸው እርምጃውን ወስደናል ብሏል።
ሁቲዎቹ አማጽያን በሚያደርሱት ጥቃት የተነሳ ቁልፍ የንግድ መስመር በሆነው በቀይ ባሕር በኩል የሚያልፉ መርከቦች የኢንሹራንስ ወጪ በእጅጉ እንዲወደድ አድርጓል። ብዙዎች መርከቦች ያንን መስመር ትተው ረጅም ጊዜ በሚወስደው በደቡባዊ አፍሪካ ጠረፍ በኩል ዞረው ማለፍ ጀምረዋል።