“በሰሜን ኮሪያ ላይ ጦርነት አላወጅንም” ሲሉ በትላንትናው ዕለት ለጋዜጠኞች የተናገሩት የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ሳራ ሃከቤ ናቸው።
“እንደ እውነቱ ከሆነ ያ አነጋገር መሠረተ ቢስ ነው” ብለዋል።
ከቃል አቀባይዋ አስተያየት ጥቂት ሰዓታት ቀደም ብሎ የቀደመውን ውንጀላ ያሰሙት፤
“ሰሜን ኮሪያ በያዘችው ዛቻና ማስፈራራት ከቀጠለች ፒዮንግያንግ የምትባል አገር አትኖርም” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በትዊተር አማካኝነት ያስተላለፉትን መልዕክት ዋቢ ያደረጉት የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ናቸው።
ሪዮ ያንግ ሆ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ተገኝተው ለጋዜጠኞች በሰጡት አስተያየት፤ “በእርግጥ ይህ አነጋገር ባሁኑ ወቅት የዩናይትድ ስቴትስን ፕሬዝዳንታዊ መንበር ከተቆናጠጡ ሰው ሲሰማ፤ ይሄ በግልጽ የጦርነት አዋጅ ነው።” ብለዋል።
የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አክለውም አገራችን ላይ መጀመሪያ ጦርነቱን ያወጀችው ዩናይትድ ስቴትስ መሆኗን የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ዓለም በሙሉ ሊያስታውስ ይገባል።” ብለዋል።
“ምንም እንኳን ሰሜን ኮሪያ ካሁን ቀደም በተደጋጋሚ ጦርነት ብታውጅም፤ አሁን ግን ወደለየለት አንዳች ቀውስ እያመራን ይመስላል፤” ያሉት በኒው ዚላንድ ዌሊንግተን የቪክቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የዓለምቀፍ ጉዳዮች አንጋፋው የፖለቲካ ጉዳዮች አጥኚ ቫን ጃክሰን ናቸው።
የቀድሞው የኮሪያ ፖሊሲ ጉዳዮች ዳይሬክተር እና የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስቴር የመከላከያ ስትራተጂ አማካሪ ለአሜሪካ ድምፅ በሰጡት በዚህ አስተያየታቸው፤
“አሁን የተባለው ጦርነት መሃል ባንሆንም፤ በምንናገራቸውም ሆነ በምንወስዳቸው ርምጃዎች ግን ጦርነት ለማስወገድ የሚያስችሉ ጥረቶችን የሚያሰናከሉና የግጭትን አይቀሬነት የሚያረጋግጡ ነገሮችን በሙሉ እያደረግን ነው።” ብለዋል።
በሌላ በኩል የሰሜን ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በበኩላቸው ፒዮንግያንግ በሰሜን ኮሪያ የአየር ክልል ውስጥ ባይገኙም የዩናይትድ ስቴትስን ስትራተጂያዊ ቦምብ ጣይ አውሮፕላኖች መትታ ትጥላለች፤ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ሀገራቸው ከሰሜን ኮሪያ ጋር ጦርነት ውስጥ አትገባም የሚል ተስፋ እንዳላቸው ትላንት በፀጥታ ጉዳዮች ጉባኤ ላይ የተናገሩት የዩናይትድ ስቴትሱ የብሔራዊ ፀጥታ ጉዳዮች አማካሪ H.R. McMaster ነገር ግን ሊሆን የሚችልበት ዕድል አለ፤ ብለዋል።