የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስ በመጪው ጥቅምት በሚካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የዲሞክራቲክ ፓርቲያቸው ዕጩ ለመሆን በቂ ድጋፍ አግኝተዋል። የፓርቲው መሪዎች በሚቀጥለው ነሃሴ ወር ከሚከፈተው የፓርቲው ብሔራዊ ጉባኤ አስቀድሞ በይፋ የፓርቲውን ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ለመሰየም ዝግጅታቸውን በማጠናቀቅ ላይ ናቸው።
አሶሲየትድ ፕሬስ ትላንት ሰኞ ማታ ባወጣው አሃዝ መሠረት ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ሆነው በፓርቲያቸው ጉባኤ ለመመረጥ የ1976 ተወካዮች አብላጫ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ካማላ ሃሪስ ከወዲሁ ከ2200 የሚበልጡ የፓርቲ ተወካዮችን ድጋፍ አግኝተዋል። አሃዙ የክፍለ ግዛቶች የፓርቲ ጽህፈት ቤቶች መግለጫዎችን እና በመጪው የፓርቲው ጉባኤ ከሚሳተፉ ተወካዮች ጋር የተደረጉ ቃለ መጠይቆችን መሠረት ያደረገ መሆኑን አሶሲየትድ ፕሬስ ጠቅሷል።
ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሃሪስ ትላንት ሰኞ ማታ በወጡት መግለጫ "ዕጩ ፕሬዚደንት ሆኜ በቅርቡ በይፋ ለመሰየም በጉጉት እጠብቃለሁ" ብለዋል።
ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ከፉክክሩ መውጣታቸውን ከማስታወቃቸው በፊትም የዲሞክራቲክ ፓርቲው መሪዎች ከጉባኤው በፊት ድምጽ ለመስጠት አቅደው ነበር። የፓርቲው መሪዎች ሂደቱን ለማጠናቀቅ ነገ ረቡዕ የሚሰበሰቡ ሲሆን የፓርቲው ብሔራዊ ኮሚቴ ሊቀመንበር ጄሚ ሐሪሰን ትላንት ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል እአአ ከነሃሴ 7 ማለትም እስከመጪው ሳምንት ረቡዕ ባሉት ቀናት ፓርቲው ፕሬዚደንታዊ ዕጩውን እንደሚመርጥ ተናግረዋል።
ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ ፕሬዚደንት ባይደን ከትላንት በስቲያ ዕሁድ ከፉክክሩ መውጣቸውን ካስታወቁ በኋላ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ለምርጫ ዘመቻቸው ከ80 ሚሊዮን ዶላር በላይ መዋጮ አሰባስበዋል።
በርካታ የዲሞክራቲክ ፓርቲው ባለሥልጣናት ለ59 ዓመቷ ምክትል ፕሬዚደንት ሐሪስ ድጋፋቸውን የገለጹላቸው ሲሆን እስካሁን ለፓርቲው እጩነት ሊፎካከራቸው የወጣ የሚታወቅ ተቀናቃኝ የለም።
የኔን ታሪክ ከትረምፕ ታሪክ አንጻር በኩራት ለማሳየት ዝግጁ ነኝ"
የኢሊኖይ አገረ ገዢ ጄ ቢ ፕሪትዝከር፥ የሚሺጋኗ ግሬቸን ዊትመር፥ የኬንተኪው አንዲ በሽር፥ የሜሪላንዱ ዌስ ሙር፥ የካሊፎርኒያው ጋቪን ኒውሰም፥ የሚኒሶታው ቲም ዎልዝ፥ እና የዊስከንስኑን ቶኒ ኤቨርስን ጨምሮ በርካታ አገረ ገዢዎች ሐሪስ ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ሆነው እንዲመረጡ ድጋፋቸውን ሰጠዋቸዋል።
የተጠቀሱት አብዛኞቹ አገረ ገዢዎች ካማላ ሃሪስ ዕጩ ሆነው ከተመረጡ ለምክትል ፕሬዚደንትነት አብረዋቸው እንዲወዳደሩ ይመርጧቸዋል በሚል ስማቸው እየተጠቀሰ ሲሆን ሃሪስ ማንን እንደሚመርጡ እስካሁን በይፋ ፍንጭ አልሰጡም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሪፐብሊካን ፓርቲው ፕሬዚደንታዊ ዕጩ ዶናልድ ትረምፕ የምርጫ ዘመቻ ባወጣው ማስታወቂያ " ካማላ የ81 ዓመቱ ጆ ባይደን በአዕምሮም በአካልም እየተዳከሙ መሆናቸውን እያወቁ ሲሸፋፍኑ ቆይተዋል በመሆኑም ይህ ውድቀት እሳቸውንም ይመለከታል" ብሏል።
ካማላ ሃሪስ ትላንት ሰኞ በተገኙበት የምርጫ ዘመቻ ዝግጅት "የኔን ታሪክ ከትረምፕ ታሪክ አንጻር በኩራት ለማሳየት ዝግጁ ነኝ" ብለዋል።
"ዶናልድ ትረምፕ የሚፈልጉት ሀገራችንን ብዙዎች አሜሪካዊያን መሉ መብት እና ነጻነት ተነፍገው ወደኖሩበት ዘመን ለመመለስ ነው። እኛ ግን ለሁሉም አሜሪካዊ ቦታ የሚሰጥ ብሩህ ቀን መምጣት እንዳለበት እናምናለን" ብለዋል።