ዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞውን የሦሪያ ማረሚያ ቤቶች ኃላፊ ታሳሪዎችን በማሰቃየት ወንጀል ተጠያቂ አደረገች

ፎቶ ፋይል፦ ከእስር የተለቀቀው የሦሪያ እሥርኛ ሰሜናዊ ምስራቅ ወጣ ብሎ ከሚገኘው ከአድራ እስር ቤት ሲወጣ ከወንድሙ ጋር ተቃቅፎ ደስታውን ይገልጣል፤ ደማስቆ፣ ሦሪያ፤ ጥር 16/2012

የቀድሞ የሦሪያ ማረሚያ ቤቶች ኃላፊ ከሥልጣን የተወገደውን የባሻር አላሳድ መንግሥት ተቃዋሚዎች በማሰቃየት ወንጀል መከሰሳቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የፍትህ ሚኒስቴር በትላንትናው ዕለት አስታወቀ።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2020 አንስቶ በዩናይትድ ስቴትስ የኖሩት የ72 ዓመቱ ሳሚር ኦስማን አልሼክ የተባሉትን ወንጀሎች የፈጸሙት፣ ታሳሪዎች ለአሰቃቂ በደል ሲዳረጉበት መቆየታቸው የተነገረውን ‘አድራ’ በሚል መጠሪያ የሚታወቀውን የደማስቆ ማዕከላዊ እስር ቤት ባስተዳደሩበት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ2005 እስከ 2008 በነበረው ጊዜ ውስጥ ነው፤ ተብሏል።

በእስር ቤቱ ከሚፈጸሙት በተጨማሪ አልሼክ በግላቸው በእስረኞች ላይ ከባድ የአካል እና የአዕምሮ ስቃይ መፈጸማቸውን፤ እንዲሁም መሰል ድርጊቶችን እንዲፈጽሙ የማረሚያ ቤቱን ሠራተኞች ማዘዛቸውን የዩናይትድ ስቴትስ አቃቤ ህግ በክሱ ዘርዝሯል።

አልሼክ እስር ቤቱን ባስተዳደሩበት ወቅት፤ እስረኞች ከጣሪያ ማገር ላይ እንዲጠለጠሉ፤ አለያም "በራሪ ምንጣፍ" የሚል ሥያሜ በተሰጠው እና ሰውነታቸውን ከወገባቸው ላይ ከፍሎ ለሁለት በማጠፍ ለከፍተኛ ሥቃይ የሚዳርግ መሳሪያ፤ አንዳንዴም የአከርካሪ አጥንታቸው እስኪሰበር ይደበደቡ ነበር ተብሏል።

በአልሼክ ላይ የቀረበው ክስ የተሰማው፤ አሳድ መንግሥታቸው እየፈራረሰ በነበረበት ወቅት ከሃገር ከኮበለሉ ቀናት በኋላ፤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሦሪያውያን ለአስርት አመታት በዘለቀው ጭቆና የደረሰባቸውን እያጤኑ በነበሩበት ወቅት ነው።