የዩክሬን ፕሬዚዳንት፣ የሩሲያ ኃይሎች የሩሲያን ወረራን አንደኛ ዓመት አስመልክቶ ወደፊት ሊገፉ ያስባሉ የሚለውን ማስጠንቀቂያ ባሰተላለፉበት ወቅት፣ የአውሮፓ ህብረት መሪዎች፣ ለዩክሬን ህዝብ ያላቸውን ድጋፍ ለመግለጽ፣ ኪየቭ ገብተዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ኡርሱላ ቮን ደ ሌይን ባስተላለፉት የትዊት መልዕክት “እዚህ ያለነው የአውሮፓ ህብረት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ፣ ከዩክሬን ህዝብ ጎን አብረን መቆማችንን ለማሳየት ነው፣ ወዳጅነታችንን ለማጥበቅና ድጋፍና ትብብራችንን ለማጠናከር ነው” ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊስ ኃላፊ ጆሴፍ ቦሬል፣ የህብረቱ ልኡካን “አገራቸውን በመከላከል ላይ ለሚገኙ ዩክሬናውያን በሙሉ ህብረቱ ያለውን ድጋፍ የሚገልጽ ጠንካራ መልዕክት ለማስተላለፍ” በኪየቭ መገኘታቸው ገልጸዋል፡፡
ቦሬል አክለውም “የአውሮፓ ህብረት የሩሲያ ጦርነት ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ ከዩክሬን ጋር ቆሟል፣ አሁንም ጦርነቱን በድል ተጠናቆ መልሶ ግንባታ እስኪሆን ድረስ አብሯችሁ ይቆማል” ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት እና የዩክሬን መሪዎች፣ ህብረቱ ለግጭቱ በሚሰጠው ምላሽ፣ መልሶ በመገንባትና የእርዳታ ጥረቶች፣ እንዲሁም በዓለም የምግብ ደህንነት እና በዩክሬን የአውሮፓ ህብረት አባልነት ማመልከቻ ዙሪያ፣ ነገ አርብ ተገናኝቶ እንደሚመክር ተመልክቷል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ፣ በየምሽቱ በሚያሰሙት የትንናት ረቡዕ ንግግራቸው፣ “ሩሲያ ወረራ በጀመረችበት የመጀመሪያው ዓመት፣ እኤአ የካቲት 24፣ በጦር ሜዳው አንዳንድ ድሎችን ማሳየት ትሞክራለች” ብለዋል፡፡
“በዚህ ሁኔታ ውስጥ፣ በተለይ ሁላችንም አንድ መሆን ይኖርብናል፣ በብሄራዊ የአገር ጥቅም ላይ በተለይ ልናተኩር ያስፈልጋል፣ ለዚህ ደግሞ በተለይ ጽናት ያስፈልገናል፡፡” ያሉት ዜለነስኪ “ሁላችንም እንደዚያ ሆነን እንደምንቆይ እተማመናለሁ” ብለዋል፡፡
ዜሌንስኪ አያይዘውም ሩሲያ በምስራቅ ዩክሬን የምታደርገውን ጥቃት የጨመረች በመሆኑ፣ “ሁኔታዎች እንዲያውም የበለጠ ከባድ ናቸው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡