ሩሲያ ማሪዮፖል ውስጥ 950 የዩክሬን ወታደሮች እጃቸውን ሰጡ ስትል ተናገረች

የዩክሬን ሃይሎች በዩክሬን-ሩሲያ ግጭት ወቅት ለሩሲያ ወታደሮች እጃቸውን ከሰጡ በኋላ ታጅበው በአውቶብስ ሲወሰዱ ይታያል

በሩሲያ ኃይሎች ተከብባ በከረመችው የዩክሬን የወደብ ከተማ ማሪዩፑል በዚህ ሳምንት 959 የዩክሬን ወታደሮች እጃቸውን ሰጥተዋል ሲል የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር ተናገረ። ባለፈው ሃያ አራት ሰአት ብቻ 690 ወታደሮች እጃቸውን ሰጥተዋል ያለ ሲሆን የዩክሬን ባለሥልጣናት ግን በሩሲያ የተሰጠውን ቁጥር አላረጋገጡም።

የዩክሬን ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር አና ማልያርሳይድ ማሪዮፑል ከተማ ውስጥ ከወደመው ብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ፍርስራሽ ውስጥ ወጥተው ለሩሲያ ኃይሎች እጃቸውን መስጥታቸውን ሰኞ ዕለት ተናግረው ነበር።

ሩሲያ በጅምላ እጅ ሰጡ ስትል ዩክሬን ሰራዊታችን የሩሲያ ኃይሎች ከማሪዮፖል እንዳያልፉ በማድረግ ተልዕኮውን አጠናቅቋል ስትል ገልጻዋለች።

የዩክሬናውያኑ ወታደሮች ዕጣ ፈንታ ምን እንደሚሆን ለግዜው ግልጽ አይደለም። አንድ የሩሲያ ባለሥልጣን በስፋት የእስረኛ ልውውጥ የመሳካቱን ዕድል አጠራጣሪ አድርገው ገልጸውታል።

ሩሲያ ከውጊያው በፊት 430፣000 ህዝብ ይኖርባት የነበረችውን አዞቭ ባህር ዳርቻ የምትገኘውን ማሪዩፑልን መያዟ ከሦስት ወራት በፊት በከፈተችው ወረራ ትልቁ ድሏ ነው ተብሏል።

ሩሲያ ምስራቅ ዩክሬን ውስጥም ተጨማሪ ግዛት ለመያዝም ሆነ የፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪን መንግሥት ለመገልበጥ ወይም ዋና ከተማዋን ኪየቭን ለመቆጣጠር የያዘችው ሙከራ አልተሳካላትም።

የሩሲያ ኃይሎች ሲደበድቧት በሰነበቱት ማሪዮፖል ውስጥ ቁጥሩ 20,000 የሚገመት ህዝብ መግደላቸውን ዪክሬን የገለጸች ሲሆን እና ከተማዋን አውድመዋታል።

የማሪዮፕል በሩሲያ እጅ መውደቅ በጦርነቱ የሚኖረውን አንድምታ ማወቅ እንደሚያስቸግር የገለጹት የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጃን ከርቢ ማሪዮፖል ትልቅ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴው የሚደረግባት ወደብ ከመሆኑዋም በስተቀር መልክአ ምድራዊ አቀማመጧም በምስራቅ በኩል ለሚካሄደው ጦርነት አስተዋጻኦ እንዳለው አስታውሰዋል።

በሌላ በኩል ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት አባልነት ማመልከቻቸውን አስገብተዋል። የሁለቱ ሀገሮች አምባሳደሮች ብረሰልስ ላይ ከኔቶ ዋና ጸኃፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ ጋር ስብሰባ ማደረጋቸው ተዘግቧል። ማመልከቻቸው የሰላሳውንም የህብረቱን አባላ ሀገሮች ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል።

ቱርክ እንደምትቃወም ገልጻለች። የቱርክ ፕሬዚደንት ሬቼፕ ታይፕ ኤርዶዋን ስዊድን እና ፊንላንድን ለአሸባሪዎች መሸሸጊያ ሰጠተዋል ማዕቀብ ጥለውብናል በማለት ይወነጅሉዋቸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ለጋዜጠኞች በሰጡት ቃል የኔቶ አጋሮች በሁለቱ አገሮች አባልነት ጉዳይ ውይይት አድርገውበት ጠንካራ ሥምምነት መኖሩንና እንደዚሁ ይቀጥላል ብለው እንደሚተማመኑ ገልጸዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የገንዘብ ሚኒስትር ጃኔት ዬለን ትናንት ብረሰልስ ውስጥ ባደረጉት ንግግር የኔቶ አባል ሀገሮች ለዩክሬን ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዲሰጡ አሳስበዋል።

ዩክሬን በሩሲያ ወረራ ከደረሰባት ጉዳት እንድታገግም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓ ሀገሮችን ለመገንባት እንደተደረገው ያለ ጥረት ማስፈለጉ አይቀሬ ነው ብለዋል።

የገንዘብ ሚኒስትሯ በንግግራቸው ዩናይትድ ስቴትስ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የአውሮፓ ሀገሮች ኢኮኖሚ እንዲያገግም ለመርዳት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር እርዳታ የሰጠችበትን ማርሻል ፕላን የተሰኘውን ዕቅድ በስሙ አይጥሩት እንጂ እሱን ማስታወሳቸው እንደሆነ ተመልክቷል።