በዩናይትድ ስቴትስ አስተናጋጅነት የተጠራው የዩክሬን ድጋፍ ጉባኤ

የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን

የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን

የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላዲሚር ፑቲን ዓለም በጠቅላላ እንደዚህ በፍጥነት እና በዕርገጠኝነት ከዩክሬን ጎን ይቆማል ብለው ፈጽሞ አልጠበቁም ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚኒስትር ተናገሩ። የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስተን ይህን ያሉት ለዩክሬን የሚደረገውን የጸጥታ ድጋፍ ለማቀናጀት ዩናይትድ ስቴትስ በጀርመን በጠራችው ጉባዔ መክፈቻ ላይ ነው።

ሎይድ ኦስተን በራምሽታይን የአየር ኃይል ሰፈር ከአርባ የሚበልጡ ሀገሮች በተካፈሉበት ጉባዔ መክፈቻ ንግግራቸው የጉባዔው ዐላማ ዩክሬን ሩሲያ በከፈተችባት ኢፍትሃዊ ወረራ እንድታሸንፍ እና በመቀጠልም የነገን ፈተናዎች እንድትወጣ ለማስቻል መሆኑን ገልጸዋል።

ጉባኤው የተጠራው የዩናይትድ ስቴትሱ የመከላከያ ሚኒስትር ኦስተን እና እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን በዩክሬን ዋና ከተማ ኪየቭ ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ነው። ሚኒስትሮቹ በኪየቭ በጉብኝታቸው ለዩክሬን ተጨማሪ ወታደራዊ እርዳታ እንሰጣለን ሌሎች አገሮችንም እናስተባብራለን በማለት ቃል ገብተዋል።

የሩሲያ ወረራ እና የጭካኔ አድራጎት ምንም ምክንያት የማይሰጠው ነው ያሉት የመከላከያ ሚኒስትሩ ዛሬ ውይይታችንን የምንጀምረው ይህን መርህ ይዘን ነው ሩሲያ በአንድ ግለሰብ ፍላጎት ይሁነኝ ብላ የከፈተችው ጦርነት ነው። ዩክሬን ግን አሉ ዲሞክራሲዋን እና ሉዐላዊነቷን እና ዜጎቹዋን ለመጠበቅ ተገድዳ የገባችበት ጦርነት ነው።

ትናንት የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ ኔቶ በተዘዋዋሪ ከሩስያ ጋር ጦርነት እያካሄደ ነው ብለው ግጭቱ ወደሶሶተኛ የዐለም ጦርነት ሊያመራ ይችላል ብለዋል። ይህንኑ ተከትሎ የዩክሬይን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌይባ በትዊተር ገጻቸው በወጡት ጽሁፍ ሩሲያ ዐለም ዩክሬንን እንዳይደግ የማስፈራራት ተስፋዋ አክትሞባታል ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶንዮ ጉቴሬዥ ዛሬ በሞስኮ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ላቭሮቭ ጋር ውይይታቸውን ሲጀምሩ በሰጡት ቃል ሩሲያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ዩክሬን ውስጥ እየሆነ ያለውን በተለያየ መንገድ የሚተረጉሙት መሆኑ እንዳለ ሆኖ ጦርነቱ ባፋጣኝ እንዲቆም እና የህዝብ ስቃይ እንዲያበቃ አሁንም ቢሆን መነጋገር ይቻላል ብለዋል።

ዋና ጸሃፊው ዛሬ ከፕሬዚዳንት ፑቲንም ጋር እንደሚነጋገሩ ተገልጿል።