የተወሰነውን እንቅስቃሴዎቻቸውን በረድ እናደርጋለን ብለው የነበሩት የሩሲያ ኃይሎች የገቡትን ቃል ማጠፋቸውን ተከትሎ የዩክሬን ፕሬዚዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ ዩናይትድ ስቴትስ ለሀገራቸው ተጨማሪ እርዳታ እንድትሰጥ በድጋሚ ተማጽነዋል።
የሩሲያ ኃይሎች የዩክሬን መዲና ኪየቭ እና ሰሜናዊዋ ቼርኒሂቭ ከተማ አካባቢን በቦምብ መደብደባቸው እና በሌሎችም አካባቢዎች ጥቃቱ መባባሱ ደም እያፋሰሰ ያለውን ጦርነት እንዲያከትም የሚደረገው ጥረት ወደፊት የመራመዱን ተስፋ ይበልጡን አጨልሞታል ተብሏል።
በውጊያው ከተጠመዱት ከተሞች መውጫ ያጡ ሰላማዊ ሰዎች የከፋ ስቃይ ላይ ሲሆኑ ሁለቱም ወገኖች ከወደብ ከተማዋ ከማሪዮፖል ሲቪሎችን ለማስወጣት ሙከራችንን እናቀጥላለን ሲሉ ዛሬ ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ተደራዳሪ ቡድን መሪ እንዳሉት የተጀመረው የሰላም ድርድር ነገ አርብ በቪዲዮ አማካይነት ይቀጥላል።
ዩናይትድ ስቴትስ ተጨማሪ እርዳታ እንድታደርግ ግፊት ለማድረግ ከትናንት በስተያ ረቡዕ ዋሺንግተንን የጎበኙት የዩክሬን የምክር ቤት አባላት ሀገራቸው ተጨማሪ የጦር መሳሪያ እና የገንዘብ እርዳታ እንደሚያስፈልጋት እና ሩሲያ ላይ ይበልጡን ጠበቅ ያለ ማዕቀብ እንዲጣል ጠይቀዋል።