አሜሪካ በስዊዘርላንድ የአፍጋን ፈንድ አቋቋመች

  • ቪኦኤ ዜና
ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት

ፎቶ ፋይል፦ የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት በአሜሪካ ባንኮች ተይዞ የነበረ 3.5 ቢሊዮን የአፍጋኒስታን ተቀማጭ ገንዘብን በመጠቀም የአፍጋኒስታንን ኢኮኖሚ ለማረጋጋት በሚል በስዊዘርላንድ ፈንድ ማቋቋሙን አስታውቋል።

በታሊባን የሚመራው የአፍጋኒስታን መንግሥት በአሜሪካ ባንኮች የሚገኝና በዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት የታገደ በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ተቀማጭ ገንዘብ እንዲመለስለት ሲወተውት ቆይቷል።

የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት እንዳስታወቀው በስዊዘርላንድ የተቋቋመው ፈንድ የአፍጋኒስታንን ሃብት ለመጠበቅና ግንዘቡ ለታለሙ ጉዳዮች እንዲውል ለማድረግ ያለመ ነው።

የባለአደራዎች ቦርድ ፈሰሱን ያስተዳድራል መባሉንም የቪኦኤው ክሪስ ሃናስ ሪፖርት ጠቁሟል።

ገንዘቡ የኤሌክትሪክ አይል ለማስገባት፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማት ዕዳ ክፍያ እና አፍጋኒስታን ለልማት ዕርዳታ ብቁ እንድትሆን ዋስትና የሚውል ነው ተብሏል።

የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ምክትል ጸሃፊ ዋሊ አደየሞ በጻፉት ደብዳቤ እንዳሉት ገንዘቡ ወደ አፍጋኒስታን ማዕከላዊ ባንክ ቢላክ፣ ለአፍጋን ሰዎች ጠቀሜታ ላይውል ይችላል የሚል ሥጋትን ይፈጥራል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አለመረጋጋት በሰፈነባት ፓንሺር ግዛት ውስጥ ያሉ አማጺያንን “ለማጽዳት” ባለው ዘመቻ በደርዘን የሚቆጠሩ አማጺያንን መግደሉንና በርካቶችን መማረኩን የታሊባን ፀጥታ ኃይል አስታውቋል።

የታሊባን ዋና ቃል አቀባይ ዛቢሁላ ሙጃሂድ ዛሬ ለቪኦኤ እንደተናገሩት ዘመቻው የተካሄደው ተራራማ በሆኑ ሦስት አካባቢዎች ሲሆን ይህም አማጺያኑ የህዝቡን ደህንነት እንዳያውኩ ለመከላከል ነው ብለዋል።

ተቺዎች እንደሚሉት ግን ዘመቻው የ”ብሄራዊ ተቃውሞ ግንባር” ወይም ኤንአርኤፍ የተሰኘውና እያደገ የመጣውን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ታሊባን መቋቋም እንደተሳነው ያመላከተ ነው።

“ታሊባን ስምንት አማጺያንን ከያዘ በኋላ ረሽኗቸዋል ሲሉ” የኤንአርኤፍ ቃል አቀባይ ሲብጋቱላ አህማዲ በትዊተር ታሊባንን ወንጅለዋል።

ሁለቱም ወገኖች የሚሉትን ቪኦኤ ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ አልቻለም።