ዩናይትድ ስቴትስ እአአ መስከረም 11/2001 ወደ 3,000 የሚጠጉ ሰዎችን የገደለውን የሽብር ጥቃት 23ኛ ዓመት ዛሬ ረቡዕ አስባለች።
በኒው ዮርክ የሽብር ጥቃቱ ሰለባዎች ቤተሰቦች፣ የተጠለፈው አውሮፕላን ተከስክሶባቸው የወደሙት፣ ሁለቱ የቀድሞ የዓለም ንግድ ማእከል ህንጻዎች በነበሩበት “ግራውንድ ዜሮ” ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ተገኝተው፣ በአደጋው ህይወታቸው ያለፉትን ሰዎች አስበዋል፡፡
በመታሰቢያ ስነ ሥርዓቱ ላይ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝዳንት ካምላ ሄሪስ ከቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትረምፕ እና በተቃናቃኞቹ ፖለቲከኞች መካከል ቆመው ከነበሩት ከቀድሞው የኒው ዮርክ ከንቲባ ማይክ ብሉምበርግ ጋር በአንድነት ተገኝተዋል።
ፊላዴልፊያ ውስጥ ውጥረት የተሞላበትን የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ክርክራቸውን ባጠናቀቁ 12 ሰዓታት ባልሞላ ጊዜ ዳግመኛ የተገናኙት ሃሪስ እና ትረምፕ ተጨባብጠው አጭር ሰላምታ ተለዋውጠዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ባይደንን እና ምክትላቸው ከካምላ ሄሪስ እአአ በመስከረም 11 በአልቃይዳ የተጠለፈው ሌላኛው አውሮፕላን ወደቆ የተከሰከሰበትን በፔንስልቬንያ ግዛት ሻንክስቪል አካባቢ የሚገኙ የገጠር ማኅበረሰብ አባላትን ጎብኝተዋል፡፡
ከዚያም በመቀጠል ባይደን እና ሄሪስ ያቀኑት አራተኛው አውሮፕላን ወድቆ ወደተከሰከሰበት ከዋሽንግተን ወጣ ብሎ ወደ ሚገኘው የመከላከያ ሚኒስቴር ህንጻ ወይም ፔንታጎን ነው፡፡
ባይደን በአደጋው የተሰውትን 2,977 ሰዎች ህይወት ለማስታወስ ባሰፈሩት ማስታወሻ “የዛሬ 23 ዓመት በዚህች ዕለት አሸባሪዎች መንፈሳችንን መስበር እና ሊያንበረክኩን እንደሚችሉ አምነው ነበር፣ ነገር ግን ተሳስተዋል፡፡ ሁልጊዜም ይሳሳታሉ” ብለዋል፡፡ ባይደን አክለውም “በጨለመብን ሰዓት ብርሃን እናገኛለን፣ በአስፈሪው ሰዓት ሀገራችንን ለመጠበቅና እርስ በርስ ለመረዳዳት አብረን ተሰብስበናል፡፡ አሸባሪዎቹ ቀደሞውኑም ዒላማ ያደረጉን በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በነጻነታችን በዲሞክራሲያችን እና በአንድነታችን ምክንያት ነው፡፡” በማለት ተናግረዋል፡፡