አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ ከጣለቻቸው ገደቦች ጥቂቶቹን ማንሣቷን የመብቶች ድርጅቶች ተቃወሙት

የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት

ዩናይትድ ስቴትስ፣ በኢትዮጵያ ላይ ጥላቸው ከነበሩት ክልከላዎች አንዳንዶቹን ማንሣቷን፣ ሁለቱ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅቶች ተቃወሙት።

የዋይት ሐውስ የብሔራዊ ደኅንነት ቃል አቀባይ ጆን ኪርቢ፣ በኢትዮጵያ የሰብአዊ ኹኔታ ይዞታው መሻሻል ማሳየቱን በመጥቀስ፣ ርዳታን በተመለከተ የተጣሉ የተወሰኑ ገደቦችን ለማንሣት ድምዳሜ ላይ እንደተደረሰ፣ ባለፈው ሳምንት ዐርብ አስታውቀው ነበር።

አምነስቲ አኢንተርናሽናል እማ ሂውማን ራይስት ዎች ውሳኔውን ተቃውመው ፤ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ ከስምምነቱ በኋላ በትግራይ የዘር ማጭዳትን ጨምሮ ሌሎች የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች መፈፀማቸውን ጠቅሰዋል። እንዲህ ዓይነት ውሳኔም ወንጀል ፈፃሚዎች በሕግ እንዳይጠየቁ ያድረጋል ብለዋል። የመብት ድርጅቶቹ በትግራይ ስለሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ድምፃቸውን ማሰማት እንደሚቀጥሉም ገለፀዋል።

በሌላ በኩል መሻሻሉ የታየው፣ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ እንደኾነ የገለጹት ኪርቢ፣ ስምምነቱ፥ በ100 ሺሕዎች የሚቆጠሩ ሕዝቦችን ለረኀብ ያጋለጠውን፣ ሚሊዮኖችን ያፈናቀለውንና በ10 ሺሕዎች የሚገመቱትን ደግሞ የገደለውን ጦርነት አስቁሟል፤ ብለዋል።

በአጠቃላይ ሲታይ፣ የመብቶች ጥሰት መቀነስ ቢያሳይም፣ የመብት ተሟጋች ቡድኖች ግን፣ በኢትዮጵያ ሰሜን ክፍል በትግራይ የዘር ማጽዳትን የጨመሩ ሁከቶች ቀጥለዋል፤ ብሏል። “በአንዳንድ የርዳታ መስኮች የነበረውን እገዳ እያነሣን ነው፤ የምግብ ርዳታው ግን እንደቆመ ይቀጥላል፤” ያሉት ኪርቢ፣ “ውሳኔው፥ ለዘላቂ ሰላም የምናደርገውን ድጋፍ ለማጠናከር ያስችለናል፤” ሲሉ አክለዋል። የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፣ የሚሰጠው እገዛ፣ ሰላምንና እርቅን እንደሚያበረታታ ገልጿል።

“ርዳታው እንደገና የመቀጠሉ ዓላማ፣ የሰላም ስምምነቱን ተግባራዊነት ለመደገፍ እና ቀጣይነት ያለውን ሰላም ለማበረታታት ነው። ይህም፣ የተቀበሩ ፈንጂዎችን በማጽዳት፣ የሽግግር ፍትሕንና ተጠያቂነትን በማስፈን ይገለጻል፤” ሲሉ የውጭ ጉዳይ መ/ቤቱ ቃል አቀባይ መናገራቸውን፣ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል።

“ከመንግሥት አካላት ውጪ ያሉ ኃይሎች፣ በምዕራብ ትግራይ የሚፈጽሙትን ጨምሮ፣ ስለ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት የሚሰሙ ሪፖርቶች እንደሚያሳስቡን መግለጻችንንና መናገራችንን እንቀጥላለን፤” ያሉት ቃል አቀባዩ፣ “መንግሥት ሲቪሎችን ከጥቃት እንዲከላከልና ጥቃት ፈጻሚዎቹንም ተጠያቂ እንዲያደርግ እንጠይቃለን፤” ሲሉ አክለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፣ በኢኮኖሚ እና በጸጥታ ዘፎች ድጋፉን አቋርጦ እንደነበርና ለኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ድጋፍ ይሰጥ ከነበረው አጎአ(AGOA) ተብሎ ከሚጠራው ከታክስ ነፃ ንግድ ተጠቃሚነት አግዷት እንደነበር ሪፖርቱ አስታውሷል።

የዋይት ሐውሱ የብሔራዊ ጸጥታ ም/ቤት ቃል አቀባይ እንዳሉት፣ የአጎአ ጉዳይ፥ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ይፋ ከተደረገው እገዳዎችን የማንሣት ውሳኔ ውጪ ለብቻው የሚታይ ነው፤ ብለዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የንግድ ተወካይ፣ ከሰሃራ ግርጌ ያሉ አገሮች፣ የአጎአ ተጠቃሚነታቸውን ይቀጥሉ እንደኹ በየዓመቱ ይገመግማል፤ ሲሉ አክለዋል።

ባለፈው ዐርብ ይፋ የኾነውን የዩናይትድ ስቴትስ መግለጫ በተመለከተ፣ አስተያየቱን የተጠየቀው የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ወዲያውኑ መልስ አልሰጠም።

ከአንድ ወር በፊት፣ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት(USAID) እና የተመድ የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ለርዳታ የተላከው ምግብ፣ ለታሰበላቸው ተረጅዎች ቀርቶ ላልታለመለት ጉዳይ ውሏል፤ በሚል፣ የምግብ ርዳታቸውን አቋርጠው ነበር።

በአፍሪካ ቀንድ፣ ለዐሥርት ዓመታት ያልታየ የከፋ ድርቅ በመከሠቱ፣ እንዲሁም በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ሳቢያ፣ በአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ በኾነቸው አገር፣ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች የምግብ ርዳታ ይሻሉ።

ባለፈው መጋቢት ወር፣ በጦርነቱ የተሳተፉ ሁሉም ወገኖች፣ የጦር ወንጀል ፈጽመዋል፤ ስትል ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃ ነበር። ኢትዮጵያ እና ከትግራይ ታጣቂዎች ጋራ ለነበረው ጦርነት፣ ኢትዮጵያን ወግና እንደተሳተፈች የተገለጸችው ኤርትራ፣ ክሡን አስተባብለዋል።