በተባበሩት መንግስታት ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በ192 አባል ሀገሮች የተፈረመ የስደተኞችና ፍልሰተኞች አዋጅ በዓለም ዙሪያ ስደተኞችና ፍልሰተኞችን ለመንከባከብና የሰዎችን መፈናቀል ለመቀነስ ያስባል።
ኢትዮጵያ በዩናይትድ ስቴይስትና የተ.መ.ድ በስደተኞች ጉዳይ ላይ በዛሬውለት በፕሬዝደንት ባራክ ኦባማና በዋና ጸሀፊ ባን ኪ ሙን በመካሄድ ላይ ያለው ጉባዔ በባለድርሻነት ከተመረጡ ስድስት ሀገሮች አንዷ ናት። ዮርዳኖስ፣ ካናዳ፣ ሜክሲኮ፣ ሶሪያና ስዊድን የዚህ የመሪዎች ውይይት አስተባባሪዎች ሆነዋል።
በትናንትናውለት በ192 የተ.መ.ድ. አባል ሀገራት የተፈረመውን የስደተኞችና ፍልሰተኞች ስምምነት፤ እንዴት እንደሚተገብሩት በዛሬውለት በመወያየት ላይ ናቸው።
የኒውዮርኩ ስምምነት ምእራባዊያን መንግስታትና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ስደተኞችን ለሚያስጠልሉ፤ ፍልስተኞችን ደግሞ በፈቃዳቸው ወደ ሀገራቸው በመመለሱ ስራ ለሚተባበሩ ሀገሮች የገንዘብና የምግብ እርዳታ ለማቅረብ ተዘጋጅተዋል። የዩናይትድ ስቴይትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በትናንትናውለት ባደረጉት ንግግር፤ ጉዳዩ ወቅታዊና የተቀናጀ ምላሽን የሚጠይቅ እንደሆነ አሳስበዋል።
የአፍሪካ ቀንድ በርካታ ስደተኞችና ፍልስተኞች የሚመነጩበትና በግጭት፣ ጦርነትና አፋኝ አገዛዞች ዜጎች ከቀያቸው የሚሸሹበት አካባቢ ነው። ላለፉት ሃያ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ስትታመስ የቆየችው ሶማሊያ፣ በህዝብ የተመረጠ መንግስት መስርታ፣ ሁኔታዎች እየተሻሻሉ ቢመጡም፤ ለዘመናት የቆዩ የጦርነት፣ ግጭትና ተያያዥ የምጣኔ ሀብት እንዲሁም የተፈጥሮ አደጋዎች ሚሊዮኖችን ያሰደደባት ሀገር ናት።
ኤርትራ በበኩሏ በተለይ ወጣት ዜጎቿ ህይወታቸውን በህገወጥ አዘዋዋሪዎች እጅና የባህር ላይ አደጋዎች የሚያጡበት የአፍሪካ ቀንድ ሀገር ናት። የፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ የፖለቲካ አማካሪ አቶ የማነ ገብረአብ ለመንግስታቱ ድርጅት ባሰሙት ንግግር የመንግስታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።
በሰሜናዊ ኬንያ የሚገኙ የሶማሊያ ስደተኞች ጉዳይ የዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ያሳሰበ ጉዳይ ሆኗል። ሶማሊያዊያን ስደተኞችን ወደ ሀገራቸው ለመመለስ ናይሮቢ ያሳላፈችው ውሳኔ የማይቀለበስ እንድሆነ ያስታወቁት የኬንያ ምክትል ፕሬዝደንት ዊሊያም ሩቶ፣ ስደተኞችን ማስጠጋት ለኬንያ የጸጥታ እራስ ምታት እንደሆነባት ገልጸዋል።
የጅቡቲ የገንዘብና ምጣኔ ሀብት ሚኒስትሩ ሙሳ ዳዋሌ ሀገራቸው በአፍሪካ ቀንድ ፍልሰተኞችን በማስተናገድ ላይ እንደምትገኝ ገልጸው፡ ለችግሩ መፍትሄ ለማበጀት ሰዎች ከቀያቸው ሳይፈናቀሉ መረባረብ እንደሚያሻ፤ ካልሆነ ግን ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ እንደሚሄድ ገልጸዋል።
ዝርዝር ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያድምጡ።
Your browser doesn’t support HTML5