የሊብያ ተፋላሚ ኃይሎች የሰላም ሕብረት እንዲፈጥሩ ጥሪ ተደረገላቸው

በሊብያ የተ.መ.ድ. ልዩ መልዕክተኛ ማርቲን ኮብለር በትሪፖሊ ኮንፈረንስ ንግግር እያደረጉ እአአ 2015

የዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓና የመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ትናንት እሑድ ከሊብያ ተቀናቃኝ ኃይሎች ጋራ ኢጣልያ ዋና ከተማ ሮማ ውስጥ ተገናኝተው የሰላም ጥሪ አቀረቡ።

የሊብያ ተፋላሚ ኃይሎች የሰላም ሕብረት እንዲፈጥሩ ጥሪ ተደረገላቸው። ጥሪውን ያቀረቡት የዩናይትድ ስቴትስ፣ የአውሮፓና የመካከለኛው ምሥራቅ ከፍተኛ ዲፕሎማቶች ትናንት እሑድ ከሊብያ ተቀናቃኝ ኃይሎች ጋራ ኢጣልያ ዋና ከተማ ሮማ ውስጥ ተገናኝተው በተወያዩበት ጊዜ መሆኑም ታውቋል።

በዚሁ ወቅት፣ ተፋላሚ ወገኖቹ አገራቸውን ወደ ሰላም ለማምጣት የሚያስችል አንድ በተ.መ.ድ. የሚሸመገል ብሔራዊ የአንድነት ዕቅድ እንዲያጸድቁ ዲፕሎማቶቹ አሳስበዋቸዋል። ይህን አለማድረግ ለአክራሪነት በር መክፈት እንደሚሆን ያስጠነቀቁት እነዚሁ ዲፕሎማቶች፣ ዕቅዱን በመደገፍም አንድ የጋራ መግለጫ ማውጣታቸው ታውቋል።

አመጽና ውዝግብ በነበረባት የወደብ ከተማዋ ቤንጋዚ አካባቢ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች፣ ከሁለት ዓመት በኋላ ትናንት እሑድ ክፍት ሆነው ውለዋል። ተፋላሚዎቹ ወገኖችም፣ ከነገ ወዲያ ረቡዕ ሞሮኮ ላይ ሲገናኙ፣ የተኩስ አቁም ውል ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በሊብያ የተ.መ.ድ. ልዩ መልዕክተኛ ማርቲን ኮብለር፣ ስምምነቱ ገቢራዊ ይሆን ዘንድ አብዛኛዎቹ ተፋላሚ ወገኖች መፈረማቸው ጠቃሚ ነው ብለዋል።

"አንድ ነገር ግልጽ ላድርግ፤ ስምምነቱ የነገሮች ሁሉ መጨረሻ ነው ማለት አይደለም። ፈጽሞ! ያ መነሻ ነው፣ አዲሱ የአንድነት መንግሥት ለሚሰራው፣ እንደ መነሻ ነጥብ" ብለዋል።

ሊብያ፣ የረዥም ጊዜ መሪዋ ሙዓማር ጋዳፊ ከሥልጣን ከተወገዱበት እአአ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ መረጋጋት አልታየባትም። ባንድ በኩል የራሷ የሊብያ ተቀናቃኞች ለሥልጣን ይፋለማሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እራሱን እስላማዊ መንግሥት ያደረገው አይስስ (ISIS)ሊብያ ውስጥ ምሽግ ሰርቶ ሊስፋፋም እየፈለገ ነው። "ይህ አለመረጋጋት ከቀጠለ፣ ሊብያ ፍርስርሷ ይወጣል" በማለት የዩናይትድ ስቴትስ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ያስጠነቅቃሉ።

"ግጭትና አለመረጋጋት ለረዥም ጊዜ ቀጥሎ አገሪቱ ውስጥ አንድ ክፍተት ፈጥሯል። ያም ክፍተት ለአክራሪዎች ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው። አሁን ሊብያ የጀመረችው ጉዞም፣ የሕዝቧን ፍላጎት ወደሚያሟላ የመንግሥት ምሥረታ ሳይሆን፣ የሁከትን አቅጣጫ የያዘ ነው" ብለዋል።

የሚስተር ኬሪ የኢጣልያው አቻቸው ፓውሎ ገንቲሎኒ (Paolo Gentiloni) የአስቸኳይ የሰላም ምስረታን ወሳኝነት ያሰምሩበታል። ሽብርተኛነትን ለመዋጋት፣ ቁልፉ ነገር ሰላምና መረጋጋት ነው ብለዋል።

ሊብያ ህጋዊ መንግሥት ስትመሰርት፣ የ17 አገሮች ተወካዮች እንዱሁም የተመድ፣ የአውሮፓ ሕብረት፣ የአፍሪቃ ሕብረት እና የአረብ ሊግ ለመርዳት ቃል ገብተዋል።

ዛልቲካ ሆኬ (Zlatica Hoke)ተጨማሪ ዘገባ ልካልች፤ አዲሱ አበበ አቅርቦታል። ዘገባውን ከተያያዘው የድምጽ ፋይል ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

የሊብያ ተፋላሚ ኃይሎች የሰላም ሕብረት እንዲፈጥሩ ጥሪ ተደረገላቸው