ተመድ የረድኤት ሠራተኞች ጥቃት መብዛት እየተለመደ መምጣቱን አወገዘ

ፍልስጤማዊ በእስራኤል የአየር ጥቃት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ “ዎርልድ ሴንትራል ኪችን” (WCK ) የተባለው ድርጅት ሰራተኞች የተገደሉበትን ተሽከርካሪ እየተመለከተ በዲር አል በላህ፣ ማዕከላዊ ጋዛ እአአ ሚያዚያ 2/2024

ፍልስጤማዊ በእስራኤል የአየር ጥቃት የውጭ ዜጎችን ጨምሮ “ዎርልድ ሴንትራል ኪችን” (WCK ) የተባለው ድርጅት ሰራተኞች የተገደሉበትን ተሽከርካሪ እየተመለከተ በዲር አል በላህ፣ ማዕከላዊ ጋዛ እአአ ሚያዚያ 2/2024

የተባበሩት መንግስታት "ተቀባይነት የሌለው" ያለው የጥቃት መጠን በሰብአዊ ሠራተኞች ላይ የተለመደ እየሆነ መጥቷል ሲል ዛሬ ሰኞ ባወጣው መግለጫ ድርጊቱን አውግዟል።

“በዓለም ዙሪያ ጥቃት ከደረሰባቸው የረድኤት ድርጅቶች ሠራተኞች ውስጥ 280ቱ እኤአ በ2023 የተገደሉ ናቸው” ብሏል መግለጫው።

በጋዛ ያለው የእስራኤል-ሃማስ ጦርነት በዚህ ዓመት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሠራተኞች ሞት ሊያባብስ እንደሚችልም የመንግስታቱ ድርጅት አስጠንቅቋል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) ተጠባባቂ ዳይሬክተር ጆይስ ሚሱያ "በእርዳታ ሠራተኞች ላይ የሚደርሰው ጥቃት የተለመደ መሆንና ተጠያቂነት ማጣት፣ ተቀባይነት የሌለው ደንታ ቢስነት እና እጅግ በጣም ጎጂ ነው" ሲሉ የዓለም የሰብአዊነት ቀንን አስመልክቶ በወጣው መግለጫ ተናግረዋል።

"ባለፈው ዓመት 280 የእርዳታ ሠራተኞች በ33 ሀገራት የተገደሉበት እ.ኤ.አ.2023 በዓለም አቀፍ ደረጃ የሰብአዊ ማህበረሰብን ሞት በማስመዝገብ እጅግ አስከፊው ዓመት ነው" ሲል መግለጫው አመልክቷል፡፡

118 የእርዳታ ሠራተኞች ከሞቱበት እኤአ 2022 በ137 በመቶ የጨመረ መሆኑን ፣ እ.ኤ.አ. እስከ 1997 ድረስ እንደዚህ ያሉ አሃዞችን የተከታተለውን የእርዳታ ሠራተኞች ደህንነት የመረጃ ቋትን የጠቀሰው የኦቻ መግለጫ ገልጿል፡፡

“እ.ኤ.አ. በ2023 ከሞቱት ከግማሽ በላይ ወይም 163 የሚሆኑት በእስራኤል እና በሃማስ መካከል በተደረገው ጦርነት በመጀመሪያዎቹ ሶስት ወራት በጋዛ የተገደሉት የረድኤት ሰራተኞች ናቸው “ ሲል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ገልጿል።

በእርስ በርስ ግጭት በተመሰቃቀለችው ደቡብ ሱዳን 23 ሰዎች ሲሞቱ፣ እኤአ ከ2023 ጀምሮ በሁለት ተቀናቃኝ ጄኔራሎች መካከል በሚካሄደው ጦርነት ውስጥ ባለችው ሱዳን 25 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል ብሏል ።

በሟቾች ቁጥር እስከ 10ኛ ደረጃ በተሰጣቸው ሀገሮች በእስራኤል እና ሶሪያ እያንዳንዳቸው ሰባት ሰዎች ሲሞቱባቸው ኢትዮጵያ እና ዩክሬን እያንዳንዳቸው ስድስት ሰዎች ተገድለውባቸዋል፡፡

በሶማሊያ አምስት በማያንማር እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አራት ሰዎች መሞታቸውንም ዘገባው አመልክቷል።

በሁሉም ግጭቶች አብዛኞዎቹ ሟቾች ከሀገር ውስጥ የተቀጠሩ የረድኤት ሠራተኞች መሆናቸውንም ዘገባው ጠቅሷል፡፡