የመንግሥታቱ ድርጅት 4 ቢሊዮን ዶላር ዕርዳታ ለኢትዮጵያ እንዲሰጥ ጥሪ አደረገ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሓፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ

የመንግሥታቱ ድርጅት ከሌሎች አጋሮችና መንግሥታት ጋር በመሆን ከፍተኛ ዕርዳታን ለሚሹና ቢኢትዮጵያ የሚገኙ 20 ሚሊዮን ሰዎችን ለመታደግ የሚውል 4 ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንዲደረግ ጥሪ ማድረጋቸውን የዋና ጸሃፊው አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቃል አቀባይ የሆኑት ስቴፋን ጁዳሪክ አስታውቀዋል፡፡

ገንዘቡ ለምግብ ጤና እና ሌሎች እጅግ አስፈላጊ ለሆኑ አቅርቦቶች እንደሚውል ቃል አቀባዩ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

በደቡብና በምሥራቅ የአገሪቱ ክፍሎች ድርቅ ባስከተለው ችግር ምክንያት ከፍተኛ ስቃይ እየታየ መሆኑን በሰብዓዊ ተግባር ላይ የተሠማሩ አጋሮቻቸው እንደነገሯቸው ጁዳሪክ ገልጸዋል፡፡

አንዳንዶቹ እነዚህ አካባቢዎች በኮሌራ እየተጠቁ ሲሆን ፣ እስከአሁን 1 ሺህ 100 የሚሆኑ ሰዎች በበሽታው እንደተያዙ ታውቋል ብለዋል፡፡

በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ደግሞ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ሁከትን በመሸሽ ከሶማሊላንድ ወደ ኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል መግባታቸውን ጁዳሪክ አስታውሠዋል፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላም ሥምምነት ከተቋጨ ወዲህ፣ የሰብዓዊ አቅርቦቱ መሻሻሉ ቀጥሏል ያሉት ቃል አቀባዩ፣ አንዳንድ ቦታዎችን ለመድረስ ግን አሁንም አዳጋች ነው ብለዋል፡፡

ካለፈው ህዳር ወዲህ በ4ሺህ 400 የጭነት ማጓጓዣዎች የተጫነ 180 ሺህ ቶን እህልና ቁሳቁስ ትግራይ መግባቱን ጁዳሪክ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

8.5 ሚሊዮን የሚሆኑና በአፋር፣ ትግራይና አማራ ክልሎች የሚገኙ ሰዎች የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተለይተዋል ሲሉ ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡