"በፖለቲካ ወገንተኝነት መወንጀላችን እጅግ አሳስቦናል" በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት

  • ቪኦኤ ዜና

በኢትዮጵያ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መስሪያ ውስጥ የተሰማሩ የመንግሥታቱ ድርጅት መስሪያ ቤቶች እና የሰብዓዊ ረድዔት አጋሮቻቸው የሚንቀሳቀሱት ወገንተኛ የፖለቲካ አጀንዳን በመደገፍ ነው ተብሎ በቅርብ ጊዜያት በዋና ዋና መገናኛ ብዙሃን እና በማኅበራዊ መገናኛዎች የሚወጡ መግለጫዎች እጅግ አሳስበውናል ሲል ተናገረ።

የድርጅቱ የኢትዮጵያ ቢሮ ባወጣው መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና አጋሮቹ በሰብዓዊ እርዳታ ሥራቸው የሚከተሉዋቸው አራት መርሆች፤ ሰብዓዊነት፥ ገለልተኝነት ከአድላዊነት ነጻ መሆን እና ሥራን በነጻነት ማከናወን ነው ብሏል።

አስከትሎም መግለጫው እነዚህን መርሆች በማክበር ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ተቀናጅተን በሁሉም የሀገሪቱ ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ሁሉ ለችግር ተጋላጮችን ትኩረቱ ባደረገ መንገድ ወሳኝ እርዳታ በማድረግ ላይ እንገኛለን ብሏል።